አፍሪካ ለምትጋፈጣቸው ዓለም አቀፋዊ ጫናዎች አህጉራዊ መፍትሔዎች ያስፈልጋሉ – ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አፍሪካ ለምትጋፈጣቸው ዓለም አቀፋዊ ጫናዎች አህጉራዊ መፍትሔዎችን መፈለግ ይገባል አሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፡፡
በ49ኛው የአፍሪካ ሕብረት ስራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት ጉባኤ ላይ እንዳሉት፤ የአየር ንብረት ለውጥ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ችግሮች ጋር ተዳምረው ዓለምን እየፈተኑ ነው።
ለእነዚህ ዓለም አቀፋዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ መፈለግ የጉባኤው ተልዕኮ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት አህጉሪቱ በዓለም አቀፍ ተቋማት ስለሚኖራት ሚና በተገቢው ደረጃ ድምፅ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል።
አፍሪካ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛው አጋማሽ ለዓለም እድገት ሞተር ለመሆን የለውጥ ርምጃዎቿ ተገቢውን መስመር የተከተሉ መሆን እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡
ለዚህም አዲስ አፍሪካዊ የለውጥ አድማስ መፍጠር ይገባል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም የአፍሪካ ሀብት በአፍሪካዊያን ተቋማት የሚመራና ለጋራ ተጠቃሚነት እና ለአህጉራዊ ብልፅግና የሚውል መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በበኩላቸው÷ አህጉሪቱ ዛሬም ድረስ ለውጥ የሚሹ ችግሮች እየፈተኗት እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
የስራ አስፈፃሚዎች ጉባኤው ለችግሮቹ አህጉራዊ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የሚያመላክት መሆን እንዳለበት ጠቁመው፤ ሀገራት የለውጥ ጉዟቸውን ከአፍሪካ አጀንዳ 2063 ጋር በማጣጣም ሊተገብሩ ይገባል ብለዋል፡፡
ህብረቱ በዓለም አቀፍ ተቋማት አፍሪካ ሊኖራት ስለሚገባ ሚና እና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ዙሪያ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
የአፍሪካን ግቦች እውን ለማድረግ የሚያስችል ምቹ ምህዳር ለመፍጠር ሰላሟ የተረጋገጠችና ለልማት የቀረበች አህጉርን መፍጠር እንደሚገባም አመላክተዋል።
በአሸናፊ ሽብሩ