Fana: At a Speed of Life!

ምክክሩ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባህል ከመሰረቱ የሚቀይር ክስተት ነው

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር የሀገሪቱን የፖለቲካ ባህል ከስር መሰረቱ የሚቀይር ታሪካዊ ክስተት ነው።

ይህ ጅምር ከጠብ መንጃ ፖለቲካ ወደ ጠረጴዛ ውይይት፣ የጋራ መግባባት እና ሀገርን በሕዝብ ፍላጎት ወደ መገንባት ምዕራፍ ያሸጋግረናል።

ኢትዮጵያ በረጅም ዘመን ታሪኳ ውስጥ በርካታ የፖለቲካ ውጣ ውረዶችን እና የሀገር ግንባታ ፈተናዎችን አሳልፋለች።

አብዛኛውን ጊዜ የፖለቲካ ልዩነቶች እና ጥያቄዎች የሚፈቱት በኃይል እርምጃ ወይም በግጭት አዙሪት ነበር።

ይህ አውዳሚ አካሄድ ሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እና ዴሞክራሲ እንዳትጎናፀፍ ትልቅ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል።

በተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስተባባሪነት የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር ግን ይህንን የተዛባ ታሪክ የሚቀለብስ፣ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ የመፍታት እና የሰለጠነ የፖለቲካ ባህልን የማስረፅ ትልቅ ተስፋ ይዞ መጥቷል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከስር መሰረቱ እንዲቀየር ከሚያደርጉት ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ የውይይት መድረኩ ሰፊ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማግኘቱ ነው።

ከ1,234 ወረዳዎች በላይ የተሰበሰቡ አጀንዳዎች እና በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው የ4,000 ተወካዮች ጉባኤ ውሳኔዎች የህዝቡን ድምፅ ከፍ የሚያደርጉ ናቸው።

በምክክሩ ሂደት እንደ ሀገር የቆዩ አንገብጋቢ ጉዳዮች በነፃነት መነሳታቸው ፖለቲካዊ ስልጣን በኃይል ሳይሆን በሕዝብ ፍላጎት ብቻ የሚገኝበትን ስልጡን ስርዓት ለመገንባት መሠረት ይጥላል።

ሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ፍጥጫዎች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እና ማህበራዊ ትስስርን ለመገንባት የተከፈተ የጋራ መድረክ ነው።

ሂደቱ ለቀጣዩ ትውልድ የተረጋጋች እና የሰለጠነች ሀገር ለማስረከብ የሚደረግ ታሪካዊ እርምጃ በመሆኑ ሁሉም ወገን በንቃት ሊደግፈው ይገባል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.