በአረንጓዴ ዐሻራ አማካኝነት በቢሊየን የሚቆጠር ሀብት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አማካኝነት በሀገር አቀፍ ደረጃ በተቋቋሙ 120 ሺህ የችግኝ ጣቢያዎች በቢሊየን የሚቆጠር ሀብት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል አለ የግብርና ሚኒስቴር።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ኢያሱ ኤልያስ (ፕ/ር) እንዳሉት÷ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከተከናወኑ ውጤታማ ሥራዎች ጎን ለጎን የደን ጭፍጨፋ ምጣኔ ዝቅ እንዲል ተደርጓል።
በዚህም በዓመት 92 ሺህ ሄክታር የነበረው የደን ጭፍጨፋ ምጣኔ ወደ 27 ሺህ ሄክታር ዝቅ እንዲል ተደርጓል ብለዋል።
በየዓመቱ ከእርሻ ማሳዎች ላይ ይታጠብ የነበረውን የአፈር መሸርሸር ምጣኔ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን ጠቁመው÷ ቀደም ሲል በሄክታር 130 ቶን ይደርስ የነበረው የአፈር መሸርሸር ወደ 54 ቶን መውረዱን ገልጸዋል።
ወደ ወንዞችና ግድቦች ይገቡ የነበሩ የደለል መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን ገልጸው፤ ወደ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ቶን አፈርና ንጥረ ነገር ታጥቦ ይወጣ የነበረው በአሁኑ ወቅት ወደ 208 ሚሊየን ቶን ዝቅ ማለቱን አስረድተዋል።
በአቮካዶ እና በቡና ምርቶች ላይ የታየው የላቀ ምርታማነት የሀገሪቱን የወጪ ንግድ ገቢ በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን አንስተው፤ መርሐ ግብሩ ሀገሪቱ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለምታደርገው ሽግግር መሠረት መጣሉን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋሙ 120 ሺህ የችግኝ ጣቢያዎች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት በወጣቶች ማህበራትና በግል ባለሀብቶች የሚመሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።
በዘርፉ በቢሊየን የሚቆጠር ሀብት መንቀሳቀሱን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው÷ መርሐ ግብሩ ለ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር ረገድ ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማስገኘቱን አብራርተዋል።
ባለድርሻ አካላትና የህብረተሰብ ክፍሎች የተገኙ አዎንታዊ ውጤቶችን አጠናክረው በማስቀጠል ለአካባቢ ጥበቃ እና ለሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገት የድርሻቸውን እንዲወጡ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዮናስ ጌትነት