አማራ ክልል 357 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ አስገባ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2018 በጀት ዓመት ከአማራ ክልል 357 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ተልኳል አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፡፡
የአማራ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 12ኛ መደበኛ ጉባዔውን እያካሄደ ነው፡፡
አቶ አረጋ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ በዓመቱ የማዕድን ሃብትን በመለየት ለኢንዱስትሪ ልማት ግብዓት በማዋልና ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በመቆጣጠር ረገድ አበረታች ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
በዚህም በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ 357 ኪሎ ግራም ወርቅ ተሰብስቦ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረጉን ተናግረዋል።
አፈጻጸሙ የክልሉን የኢኮኖሚ አቅም ከማሳደግ ባለፈ ለውጭ ምንዛሪ ግኝትና ለፋይናንስ እንቅስቃሴ መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ጠቅሰዋል፡፡
በሌላ በኩል የክልሉን የማዕድን ሀብት ከሕገ ወጥ ምዝበራ ለመታደግ በተከናወነ ሥራ ከ133 ሺህ 500 በላይ ሜትር ኪዩብ ሕገ ወጥ ማዕድን መያዙን አስረድተዋል።
በዘርፉ ከሕገ ወጥ ምዝበራ ጋር ተያይዞ በተወሰዱ የመውረስና የማስተካከያ ርምጃዎች ከ27 ሚሊየን ብር በላይ ማዳን እንደተቻለ መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል በማዕድን ፍለጋና የክምችት ማረጋገጥ ሥራዎች በ10 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት 5 ሺህ 148 ቶን የሚገመት የብረት ማዕድን መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በ440 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ቶን ግራናይት እና 1 ነጥብ 625 ቢሊየን ቶን ጥቁር ድንጋይ ማግኘት መቻሉን ነው ያስገነዘቡት፡፡