ሕገ ወጡ ህወሓት የሰብዓዊ ዕርዳታን ለፖለቲካ ጥቅሙ እያዋለ ነው – ኮሚሽነር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ሕገ ወጡ ህወሓት የሰብዓዊ ድጋፍ ስርጭትን ለራሱ የፖለቲካ ጥቅም እያስተጓጎለ ነው አሉ፡፡
ኮሚሽነሩ ሕገ ወጡ ቡድን የሚላኩ ዕርዳታዎች ለተረጂዎች በትክክል እንዳይደርሱ በተለያዩ የቀረጥ ሥርዓቶች ውስጥ በማስገባት ዜጎች ከመሰረታዊ ድጋፍ እንዲገለሉ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ቡድኑ እየተከተለ ያለው አካሄድ የትግራይ ሕዝብን ለአደጋ የሚያጋልጥና የሚጎዳ ነው ሲሉም አስረድተዋል።
ኮሚሽነሩ አክለውም ይህ ድርጊት ቡድኑ ለራሱ የፖለቲካ ትርፍ ሲል ለሚላላካቸው አካላት ሙሉ ለሙሉ ራሱን መስጠቱን ያሳያል ብለዋል።
ሕገ ወጥ ቡድኑ በአሁኑ ወቅት የሚያሳየው ባህርይ ዛሬ የተፈጠረ ሳይሆን፣ ሕዝቡ እንዲቸገር ማድረግና የተጎዳው ሕዝብ ጮሆ እንዲነሳ ማድረግ የቡድኑ የዕድሜ ልክ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
እንደሚታወቀው ህገ ወጡ የህወሓት ቡድን በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የተገኘውን ዕድል ወደ ጎን በመተው፣ አሁንም ከሻዕቢያ ጋር በማበር የግብፅ ተላላኪነት የጦርነት ከበሮ እየደለቀ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በሰሜኑ ጦርነት ከደረሰው ከፍተኛ የሰብዓዊና የንብረት ውድመት በኋላ ሕዝቡን ከመካስ ይልቅ፣ የህገወጡ ቡድኑ መሪዎች የክልሉን ዘላቂ ሰላም ዳግም አደጋ ላይ ጥለውታል።
ቡድኑ የክልሉን ውስን ሀብት ለጦርነት ዝግጅትና ለታጣቂዎች ስምሪት እያዋለ ሲሆን÷ ታዳጊዎችንና ወጣቶችንም በግዳጅ ወደ ውትድርና በማስገባት ላይ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።
ሰላማዊ የፖለቲካ ውይይትን እንደ ድክመት የሚቆጥረው ይህ ህገ ወጥ ቡድን፣ ራሱ የሚፈጥረውን የሕዝብ ስቃይ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳየት ስልጣኑን ለማስጠበቅ እየተጠቀመበት ይገኛል።