የባሕር በር ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ልማት
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የባሕር በር ለማንኛውም ሀገር ከኢኮኖሚ፣ ከንግድ፣ ከደህንነት እና ከዓለም አቀፍ ግንኙነት አንፃር እጅግ ወሳኝ ሀብት ነው።
በዓለም ላይ አብዛኛው የዓለም ንግድ በባህር መጓጓዣ ስለሚከናወን፣ የባህር በር ያላቸው ሀገራት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነትን እንዲኖራቸው ያስችላል።
በተቃራኒው የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ከንግድ፣ የሎጂስቲክስ፣ የውጭ ጥገኝነት፣ ብሔራዊ ጸጥታ እና የመሳሰሉ ተግዳሮቶችን ይጋፈጣሉ።
ኢትዮጵያም ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ የባህር በሯን በህገ ወጥ መንገድ እንድታጣ በመደረጓ፣ በብዙ ዘርፎች ፈተናዎችን ተጋፍጣለች።
የባህር በር ያላቸው ሀገራት ምርቶችን በቀላሉ ወደ ውጭ ለመላክ እና ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት ይችላሉ፤ በዓለም ንግድ ተወዳዳሪ እንዲሆኑም ያስችላቸዋል፡፡
ይህ የንግድ መጠንን በማሳደግ የውጭ ምንዛሪ ገቢን እንዲጨምር ያግዛል።
በወደቦች አቅራቢያ የሚገኙ ፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃን በቀላሉ ማስገባት ይችላሉ፣ የተመረቱ ምርቶችንም በፍጥነት ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። ይህም ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለኢኮኖሚ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
የባህር በር በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ወጪ ቅነሳ ረገድ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል፡፡
የባህር መጓጓዣ ከአየር እና ከመንገድ መጓጓዣ ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ወጪ አለው። ስለዚህም ሸቀጦች በብዛትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቾች ለማድረስ ያስችላል።
የባህር በር ያላቸው ሀገራት በሎጂስቲክስ ምቹ በመሆናቸው የውጭ ባለሀብቶችን ይስባሉ። ይህም አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን፣ የሥራ እድሎችን እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ያበረታታል።
የባህር በር የጂኦፖለቲካ ጠቀሜታው ከፍተኛ ሲሆን ወደብ ያላቸው ሀገራት በክልላዊና በዓለም አቀፍ ንግድ ውስጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። ይህም የዲፕሎማሲ አቅማቸውን እና የኢኮኖሚ ተፅዕኖአቸውን ያጠናክራል።
ኢትዮጵያ የባህር በር በማጣቷ የተጋፈጠችው ጉዳት ዘርፈ ብዙ ሲሆን ከዚህም መካከል ከፍተኛ የማጓጓዣ፣ የወደብ ኪራይ እና ተያያዥ ወጪዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባቸውንና ወደ ውጭ የምትልካቸውን ምርቶች በጎረቤት ሀገራት ወደቦች በመጠቀም ታጓጉዛለች። ይህ ተጨማሪ የትራንስፖርት እና የወደብ ክፍያዎችን ያስከትላል።
የማጓጓዣ ወጪ ሲጨምር የሚገቡ ሸቀጦች ዋጋ ይጨምራል። ይህ በተለይ ነዳጅ፣ ማሽነሪዎቸ፣ መድሀኒቶችና ሌሎች የመሠረታዊ እቃዎች አቅርቦት እና ዋጋ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል።
ኢትዮጵያ የባህር በር አልባነቷ፣ በጎረቤት ሀገራት ወደቦችና ትራንስፖርት አገልግሎቶች ላይ እንድትመረኮዝ አድርጓታል። ይህም በጎረቤት ሀገራት የፖለቲካ እና የደህንነት ችግሮች በሚፈጠሩበት ጊዜ አቅርቦትን ሊያስተጓጉል ይችላል።
ወደብ አልባነት የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነት መቀነስ የሚያስከትል ሲሆን የማምረቻ ወጪ ሲጨምር የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም ገበያ ተወዳዳሪነታቸው ሊቀንስ ይችላል። ይህም የውጭ ምንዛሪ ገቢን እንዲቀንስ የሚያደርግ ነው።
ኢንቨስተሮችና በንግድ የተሰማሩ ድርጅቶች የማጓጓዣ ወጪ ዝቅተኛ የሆነባቸውን ሀገራት ይመርጣሉ። ስለዚህ የባህር በር አለመኖር አንዳንድ ኢንቨስትመንቶችን ሊያዘገይ ወይም ወደ ሌሎች ሀገራት እንዲዞሩ ሊያደርግ ይችላል።
የባህር በር ለሀገራት የኢኮኖሚ እድገት፣ የንግድ መስፋፋት፣ የኢንዱስትሪ ልማት፣ የውጭ ኢንቨስትመንት በመሳብ እና የክልላዊ ትስስርን በማጠናከር ረገድ ትልቅ ጠቀሜታ አለው።
ኢትዮጵያ የባህር በር በማጣቷ ከፍተኛ የማጓጓዣ ወጪ፣ የውጭ ጥገኝነት፣ የምርት ዋጋ መጨመር፣ የብሔራዊ ደህንነት እና የኢንቨስትመንት ተግዳሮቶችን ተጋፍጣለች።
ኢትዮጵያ የባህር ባለቤት ለመሆን ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሰላማዊ ውይይት፣ በኢኮኖሚያዊ ትብብር እና በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ተጠቃሚ ለመሆን ጥረቷን ቀጥላለች፡፡
ኢትዮጵያ በዘላቂነት የባህር በር ተዘግቶባት መቀጠል እንደማትችል በመገንዘብ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሀገሪቱን ፍትሃዊ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ መስራት ይገባቸዋል፡፡
መላው ኢትዮጵያዊያንም ይህ ቁልፍ ብሔራዊ ጥያቄ ምላሽ እስኪያገኝ በአንድነት መቆም ይጠበቅባቸዋል ፡፡
በቴዎድሮስ ሳህለ