Fana: At a Speed of Life!

ሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያን አንድነት እና ክብር የሚያጸና ነው – የሃይማኖት አባቶች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ የምክክር ጉባዔው የኢትዮጵያን አንድነት እና ክብር የሚያጸና ነው አሉ ተመካካሪ የሃይማኖት አባቶች፡፡
ተመካካሪዎች÷ የምክክር ሂደቱ አሳታፊ፣ አካታችና ነፃ ሆኖ መካሄዱ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ሀገራዊ መግባባትና ጠንካራ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ ተስፋ ሰጪ አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡ ተመካካሪዎች መካከል መልዓከ ሕይወት አባ ወልደ ዮሐንስ ሰይፉ÷ በዚህ ምክክር ያልተወከለ ኢትዮጵያዊ የለም ብለዋል።
ምክክሩ እርስ በርስ ይበልጥ እንድንተዋወቅ እያደረገን ነው ፤ሂደቱ አንዱ የሌላውን ሐሳብ ሳይነቅፍ፣ ፍጹም መከባበርና መተሳሰብ በሰፈነበት ሁኔታ እየተካሄደ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ይህም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ፍቅር፣ ሰላምና ልማት የሚፈልግ መሆኑን ከመገንዘብ ባለፈ ሰላሟ የተጠበቀ፣ አረንጓዴና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ወሳኝ አዲስ ምዕራፍ መሆኑን አመልክተዋል።
የምክክር ሂደቱ በአካታችነቱና አሳታፊነቱ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ተመካካሪ አብዱልመጂድ ጃፋር ናቸው።
“ይዘን የመጣነው የሀገር ኃላፊነት ነው፤ በመሆኑም ስለ ሀገራችን ሰላም፣ ልማትና እድገት ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ ምክክር እያደረግን እንገኛለን” ሲሉ ተናግረዋል።
ለሀገር በሚበጁ ጉዳዮች ላይ ተስፋ ሰጪ ውይይቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ያመላከቱት ተመካካሪው፤ በሀገራችን የጋራ መግባባት ከተፈጠረ ሌላ የሚጎድል ነገር አለመኖሩን ጠቅሰዋል።
ሐሳባቸውን በነጻነት መግለጻቸውን በማንሳት፣ ከዚህ ምክክር በኋላ ሀገራችን ትኩረት በልማት ላይ ብቻ እንድታደርግ ትልቅ እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላኛው ተመካካሪ ጻዲቁ አብዶ በበኩላቸው÷ ለአንድ ሀገር ዘላቂ መረጋጋትና ለጠንካራ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ መሠረት በሚሆኑ ዐበይት ጉዳዮች ላይ በሰለጠነ መንገድ ሐሳብ እየተለዋወጡ መሆናቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።
የምክክር ሂደቱ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት ባህልን የሚያጎለብትና ለትውልድ የሚሻገር ሰላምን የሚገነባ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ምክክሩ ፍጹም የመደማመጥና ቤተሰባዊ በሆነ መንገድ እየተካሄደ ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው ተመካካሪ አባ አማኑኤል ዮሴፍ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያን ወደ ፊት የሚያሻግሩ ሐሳቦች ተነስተው በነጻነት ምክክር እየተደረገባቸው እንደሚገኝም አመልክተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.