ዲጂታል በጎነት፣ ሰው ተኮር ውጤቶችን ለማስቀጠል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ የዜጎችን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለመ “6400 A” የዲጂታል በጎነት ፕሮጀክት ይፋ ተደርጓል፡፡
የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በዘላቂነት ለማቃለል የሚያስችለውን ፕሮጀክት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር አዘጋጅተውታል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ም/ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ በዚህ ወቅት ÷ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመዲናዋ ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለውና የበርካታ ተጋላጭ የሕብረተሰብ ክፍሎችን እንባ ያበስንበት ፕሮግራም ነው ብለዋል፡፡
የዲጂታል ፕላትፎርሙ ሃብትን ከብክነት በመታደግና ለታለመለት ዓላማ በማዋል የበርካታ ዜጎችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ማቃለል እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡
የከተማዋ የልማት አቅጣጫ የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው÷ በድህነት መኖር ተፈጥሯዊ ስሪታችን ባለመሆኑ የጋራ ችግራችንን ተባብረን መፍታት አለብን ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የሕብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ይመር ከበደ በበኩላቸው ÷ የዜጎችን የኑሮ ጫና የሚያቃልሉ ዘርፈ ብዙ ግቦች ተቀርፀው በውጤታማነት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በመደመር መንግሥት በጎነት የከተማዋ ዋና መገለጫና የሕብረተሰቡ እሴት እንዲሆን በማድረግ ረገድ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡
የ6400 A ዲጂታል በጎነት ፕሮጀክት በለውጡ ዓመታት የተገኙ ሰው ተኮር ውጤቶችን ለማስቀጠል እንደሚያግዝ አውስተዋል፡፡
ዜጎች ወደ 6400 “A”ን በመላክና በቀን 1 ብር በመለገስ የከተማ አስተዳደሩን በጎ ፈቃድ አገልግሎት ግብ ለማሳካት የበኩላቸውን እንዲወጡ ተጠይቋል፡፡