Fana: At a Speed of Life!

በሊባኖስ 18 በእስር ላይ የነበሩ ሰዎችን ጨምሮ 90 ኢትዮጵያውያን ተመለሱ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 26፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሊባኖስ 18 በእስር ላይ የነበሩ ሰዎችን ጨምሮ 90 ኢትዮጵያውያን መመለሳቸውን ሊባኖስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤቱ በሊባኖስ 2 እስር ቤቶች ታስረው የነበሩ 19 ኢትዮጵያውያንን ከፍርድ ቤቶችና እስር ቤቶቹ ጋር በመነጋገርና በማስፈታት፤ ከእነዚህም 18 ሰዎች የመውጫ ቪዛ ተሰርቶላቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ማድረጉን አስታውቋል።

በሌላ በኩል በ8ኛ ዙር የትራንስፖርት ወጪዎችን በራሳቸው በመሸፈን ወደ አገር ቤት ለመጓዝ ተመዝግበው በመጠባበቅ ላይ የነበሩ ዜጎችም የጉዞ ሰነዶቻቸውን በማዘጋጀትና ከሊባኖስ ኢሚግሬሽን የመውጫ ቪዛ እንዲያገኙ በማድረግ 71 ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል ብሏል።

በተጨማሪም ሆስፒታል ውስጥ ህክምናዋን ስትከታተል የነበረች አንድ ኢትዮጵያዊትም በቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤቱና በኢትዮጵያ ኮሙኒቲ ማህበር ትብብር እርዳታ ሲደግላት ቆይታ ወደ ኢትዮጵያ እንድትመለስ ተደርጓል።

በአጠቃላይ በዛሬው እለት 90 ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን የገለፀው ጽህፈት ቤቱ፥ ሁሉም ተመላሾች የኮሮና ቫይረስ ምርመራዎችን አድርገው ነጻ መሆናቸው መረጋገጡም አስታውቋል።
 
በተመሳሳይ ከዛሬ ማታ ጀምሮ በመጭዎቹ ቀናት 155 ዜጎች ወደ ሀገር እንደሚመለሱ ከኢትዮጵያ ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.