በአማራ ክልል የተሰሩት የልማት ስራዎች ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአማራ ክልል በተለያዩ ዘርፎች የተሰሩት የልማት ስራዎች ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ነው አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ጋር ባደረጉት ቆይታ አድንዳሉት፤ የፕሪቶሪያ ስምምነት ለአማራ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም አካባቢዎች ጥቅም ያስገኘ ነው፡፡
በአማራ ክልል የኮሪደር ልማት በ32 ከተሞች እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ የትናንት ባህርዳር እና የዛሬዋ ባህርዳር ልዩነታቸው ግልጽ ነው ብለዋል፡፡
ትናንት የነበረችው ጎንደር እና ዛሬ ያለችው ጎንደር በየትኛውም መስፈርት የሚለኩ አይደሉም ሲሉም አብራርተዋል፡፡
ወልዲያ፣ ኮምቦልቻ፣ ደብረ ብርሃን እና ደሴን ጨምሮ ሌሎች ከተሞች እንደ አቅማቸው በስፋት የኮሪደር ልማት እየተሰራላቸው መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
በዚህ ውስጥ የኑሮ ዘዴን የመቀየር ልምምድ፣ ለዕድገት መጨመር ያለ ጉጉት እና ፈጠራ መኖሩን አስረድተዋል፡፡
በአማራ ክልል የኤሌክትሪክ ሽፋን በለውጡ ማግስት 25 በመቶ እንደነበር ገልጸው፤ አሁን ከ40 በመቶ በላይ ከፍ ብሏል ነው ያሉት፡፡
ከዚህ በላይ ሊሰራ ይገባል፤ ለጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የተሄደበት ርቀት ግን በቀላሉ የሚታይ አይደለም ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
በዲጂታል ኢኮኖሚ በአማራ ክልል ብዙ እመርታ መምጣቱን አንስተው፤ 5 ሚሊየን ኮደርስ እናሰልጥን ብለን በጀመረው የዲጂታል ዘመቻ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ሰዎች ከአማራ ክልል መሰልጠናቸውን አመልክተዋል፡፡
ከለውጡ በኋላ ወደ አምስት ከተሞች የ5ጂ ኢንተርኔት በአማራ ክልል ተጠቃሚ ሆነዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከ200 በላይ ከተሞች ደግሞ በክልሉ የ4ጂ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ከለውጡ ወዲህ በዲጂታል ኢኮኖሚ፣ በኤሌክትሪክ፣ በቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በግድቦች፣ በመጠጥ ውሃ፣ በጤና፣ በትምህርት ባለፉት ዓመታት የተሰራው ስራ ከዚያ በፊት ለ20 ዓመታት ከተሰራው ስራ የሚበልጥ እንጂ የሚያንስ አይደለም ብለዋል፡፡
ይሄንን ጉዳይ በቀሪው ጊዜ አልቀንና አስፍተን ከሰራን የአማራ የመልማት እና የመጠቀም ጥያቄዎች በተሟላ መልኩ ምላሽ እያገኙ ይሄዳሉ ነው ያሉት፡፡
የፕሪቶሪያ ስምምነት ለትግራይ፣ ለአማራ፣ ለአፋር በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ያስገኘው ነገር የጥይት ድምጽ እንዳንሰማ ማድረግና ወደ ልማት እንድናተኩር ያደረገ ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡
የጥይት ድምጽ እንዳንሰማ ማድረጋችን እና ወደ ልማት መዞራችን አማራን በምንም መስፈርት ሊጎዳ አይችልም ነው ያሉት፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ