ቡና እና አረንጓዴ ዐሻራ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የቡና ምርት ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በሦስት እጥፍ እድገት አስመዝግቧል አለ የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ እንደገለጹት፥ በቡና ምርትና ምርታማነት ለተመዘገበው እድገት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከፍተኛ ድርሻ አበርክቷል፡፡
ከአምስት ዓመት በፊት ዓመታዊ የቡና ምርት 550 ሺህ ሜትሪክ ቶን እንደነበር አስታውሰው፥ ዘንድሮ በሦስት እጥፍ አድጎ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ምርት ተገኝቷል ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ ቡና በባህሪው ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፥ በአረንጓዴ ዐሻራ የተተከሉት ችግኞች ለቡና ተስማሚ የአየር ሁኔታ መፍጠራቸውን አስረድተዋል፡፡
ከሦስትና አራት ዓመታት በፊት የተተከሉ የቡና ችግኞች ዛሬ ላይ ምርት መስጠት መጀመራቸውን ገልጸው፥ እነዚህ አዳዲስ ቡናዎች የጥራት ደረጃቸው የተሻለ ነው ብለዋል፡፡
በመጪዎቹ ዓመታት የሚኖሩ የአየር ንብረት ሁኔታዎች ለቡና ምቹ አለመሆናቸውን በጥናት መመላከቱን የገለጹ ሲሆን፥ ኢትዮጵያ ግን በአረንጓዴ ዐሻራ አማካኝነት ለቡና ተስማሚ ከባቢ እየፈጠረች ነው ብለዋል፡፡
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻፊ ዑመር በበኩላቸው፥ በዚህ ዓመት ብቻ ከቡና የወጪ ንግድ ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንዲገኝ አረንጓዴ ዐሻራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አንስተዋል፡፡
በአረንጓዴ ዐሻራ በየዓመቱ እየተተከሉ ያሉት በቢሊየን የሚቆጠሩ ችግኞች የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ የደን ሽፋን እንዲጨምር አስችለዋል፡፡