Fana: At a Speed of Life!

ምክክሩ በሚፈጥረው መደላድል የተሟላ የፖለቲካ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን ትግበራን ለማሳካት ይሰራል – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ ምክክር በሚፈጥረው መደላድል የተሟላ የፖለቲካ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን ትግበራን ለማሳካት ይሰራል አሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋና ጽ/ቤቱ ኃላፊ አደም ፋራህ።

የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት የ2018 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት የእቅድ ትውውቅ መድረክ ተካሂዷል፡፡

አቶ አደም ፋራህ በመድረኩ እንዳሉት፤ ባለፉት ዓመታት በተካሄደው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እና የዲፕሎማሲ ዘርፎች ሰፋፊ የሪፎርም ስራዎች አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል፡፡

በቀጣይም ሀገራዊ ምክክር የሚፈጥረውን መደላድል በመጠቀም ከሪፎርም ወደ ተሟላ የፖለቲካ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን ትግበራ ለመግባት የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጽንፈኝነትን በመታገልና የትስስር ትርክት እንዲጎለበት ለማድረግ እንዲሁም ጠንካራ ተቋማትን ለመፍጠር የተጀመሩ የስታንዳርዳይዜሽን ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡

በብልጽግና ፓርቲ የሚመራው የመደመር መንግሥት ጠንካራ መንግሥት እና ጠንካራ ሀገር መገንባት የሚያስችሉ ውጤታማ የፓርቲ ስራዎችን ማከናወን መቻሉን አብራርተዋል፡፡

አመራሩንና አባሉን ጨምሮ ሁሉንም መዋቅር በማነቃነቅ ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች መከናወናቸውንም ገልጸዋል።

በየደረጃው ያለው አመራርና አባል የተሰጠውን ሃላፊነት በጥራትና በውጤታማነት ሊፈጽም ይገባል ነው ያሉት።

የጽ/ቤቱ አመራርና ሰራተኛ ለተመዘገበው ከፍተኛ ውጤት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና ማቅረባቸውን የፓርቲው መረጃ አመልክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.