በኦሮሚያ ክልል ሕገ ወጥ ንግድን ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ሕገ ወጥ ንግድን በዘላቂነት ለመግታት በትኩረት እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ንግድ ቢሮ።
የክልሉን ንግድ ሥርዓት ከሕገ ወጥ አሠራር የጸዳ፣ ዘመናዊና ፈጣን ለማድረግ ያለመ የምክክር መድረክ በአሰላ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
የቢሮው ም/ሃላፊ ተስፋዬ ገሾ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ሕገ ወጥ ንግድ የንግድ ዘርፉን ተዋናዮች፣ ሕብረተሰቡን እንዲሁም የሀገርን ኢኮኖሚ የሚጎዳ ተግባር ነው፡፡
በክልሉ የሚስተዋሉ ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለመከላከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅትና በቁርጠኝነት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በተለይም በዘርፉ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ የገበያ አለመረጋጋት በሚፈጥሩ ሕገ ወጥ ነጋዴዎችና ደላላዎች ላይ ርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መሰል ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በዘላቂነት ለመቆጣጠርም ነጋዴዎች፣ ሕብረተሰቡ እና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአሰላ ከተማ ከንቲባ ስሜ ጸጋዬ በበኩላቸው ÷ በሕገ ወጥ ንግድ ላይ የተሰማሩ ዜጎች ወደ ትክክለኛው የንግድ መስመር እንዲመለሱ አስተማሪና ሕጋዊ ርምጃ መውሰዱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
በንግድ ሥራዎች ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ የወጡ የንግድ አዋጆችን በተግባር ማዋልና ግንዛቤ መፍጠር ላይ በትኩረት ይሰራል ያሉት ደግሞ የአሰላ ከተማ ንግድ ጽ/ቤት ኃላፊ ሙዘይን አማን ናቸው፡፡
በሊያ ዱጉማ