የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተቋማት ባህል ወደ መሆን ተሸጋግሯል – ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት የተቋማት ባህል ወደ መሆን ተሸጋግሯል አሉ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የዘንድሮውን የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብር በሲዳማ ክልል ሸበዲኖ ወረዳ ዲላንአንፈራራ ቀበሌ አከናውኗል።
ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ በየዓመቱ በተለያዩ ክልሎች የሚተገበረው የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘንድሮም ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በዕለቱ በተካሄደው መርሐ ግብር 7 የአቅመ ደካሞች ቤቶች መታደሳቸውን፣ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 50 ሺህ ችግኞች መተከላቸውን እንዲሁም የደም ልገሳና የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
የሲዳማ ክልል የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ከበደ ጋኖሌ (ኢ/ር) በበኩላቸው፤ ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ በክልሉ የውሃ ተደራሽነትን ለማስፋፋትና የታዳሽ ኃይል ልማትን ለማፋጠን ያከናወናቸው ሥራዎች ስኬታማ እንደነበሩ አንስተዋል።
ከዚህ ጎን ለጎንም የማህበረሰቡን ችግር አቅም በፈቀደ መጠን ለማቃለል ሚኒስቴሩ የበጎ ፈቃድ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው፤ ምስጋና አቅርበዋል።
በጎህ ንጉሱ