ለዘመናት ሲጓተቱ የቆዩ የልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነት እየተከናወኑ ነው – አቶ አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በክልሉ ለዘመናት ሲጓተቱ የቆዩ የልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነት እየተከናወኑ ነው አሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የባሕር ዳር ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲሱን ተርሚናል መርቀው አገልግሎት አስጀምረዋል፡፡
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት ÷ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በክልሉ በርካታ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በተለይም በግብርና ልማት ማሻሻያ ላይ ያተኮሩ ሥራዎች በሰፊው መከናወናቸውን ጠቁመው ÷ የቱሪዝም ዘርፉን የሚያነቃቁ ታላላቅ የቱሪዝም መዳረሻዎች ተገንብተዋል ብለዋል፡፡
የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት እና የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት በቅርቡ ከተገነቡት የቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል ስለመሆናቸው በአብነት አንስተዋል።
አቶ አረጋ ከተሞች ለነዋሪዎች የተመቹ እንዲሆኑ ሥራዎች መሰራታቸውንና በባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻ እና በወልድያ ተስፋ ሰጭ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል።
ከደጃዝማች በላይ ዘለቀ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አዲሱ ተርሚናል በተጨማሪ ቀደም ሲል በደብረ ማርቆስ እና ኮምቦልቻ የተገነቡት የአውሮፕላን ማረፊያዎች የቱሪዝም እና የኢንቨስትመንት መግቢያ መስኮቶች ሆነዋል ነው ያሉት።