አቶ ጌታቸው ረዳ ከኔዘርላንድስ የውጭ ንግድና የልማት ትብብር ሚኒስትር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ ከኔዘርላንድስ የውጭ ንግድና የልማት ትብብር ሚኒስትር ስጆርድ ስጆርድስማ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም በሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት እና የጋራ ትኩረት በሚሹ ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ÷ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና በተለይም በሱዳን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ እና ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምን ለማስፈን እያደረገች ያለውን ጥረት አስመልክተው ገለጻ አድርገዋል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ እና ኔዘርላንድስ መካከል ባለው የሁለትዮሽ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና የኢኮኖሚ ትብብር ዙሪያ ተወያይተዋል።
ስጆርድ ስጆርድስማ በበኩላቸው÷ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኢንቨስትመንት እና የኢኮኖሚ ትብብር ለማስፋፋት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል።
የሁለቱን ሀገራት አጋርነት በተለያዩ ዘርፎች ይበልጥ ለማጠናከር የከፍተኛ ባለሥልጣናት ውይይት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል።
ውይይቱ ከ81ኛው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን መካሄዱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።