የኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነትና አቅም ግንባታ ስኬት ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን ነው – ቤኒን
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በሳይበር ደህንነት እና አቅም ግንባታ ያስመዘገበችው ስኬት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው አሉ የቤኒን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና ኢኖቬሽን ሚኒስትር ማሁና አክፕሎጋን (ዶ/ር)።
በሚኒስትሩ የተመራ ልዑክ ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የቴክኖሎጂ ልማትና የዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ካከናወነቻቸው ሥራዎች ተሞክሮ ለመጋራት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርን ጎብኝቷል።
የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ የልዑካን ቡድኑን ተቀብለው ተቋሙ የሀገርን የዲጂታል ሉዓላዊነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚያከናውናቸው ሥራዎች ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል፡፡
ከጉብኝቱ በኋላም ሚኒስትሮቹ በሳይበር ደህንነት፣ በሀገር በቀል ቴክኖሎጂ ልማት እና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፎች በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
ማሁና አክፕሎጋን (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ በሳይበር ጸጥታና በአቅም ግንባታ ያስመዘገበችው ስኬት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው።
በተለይም በኢመደአ ስር የሚገኘውን ኤሮአባይ የድሮን ማምረቻ ማዕከል ጨምሮ አዳዲስ ፈጠራዎች አስደናቂ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይ በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለው የዲጂታል ትብብር ማዕቀፍ ውስጥ በጋራ ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለ መግለጻቸውን የአስተዳደሩ መረጃ ያመላክታል።