Fana: At a Speed of Life!

ነፍጥ ያልነካው መፍትሔ፤ ንግግር የፈነጠቀው ተስፋ

ኢትዮጵያ ታሪካዊና ዘላቂ ሀገራዊ መፍትሔ ለማምጣት የታለመውን ሀገራዊ የምክክር ሒደት በማካሄድ ላይ ትገኛለች።

ባለፉት አራት ዓመታት አጀንዳዎችን በማሰባሰብና ዝግጅት በማድረግ የቆየው ይህ ታላቅ ጉባዔ፣ በአሁኑ ወቅት የበርካታ ወገኖችን ተሳትፎ እያስተናገደ በውይይት ምዕራፍ ላይ ይገኛል።

በዚህ ታሪካዊ የምክክር መድረክ ከተሳተፉት መካከል ቀደም ሲል በትጥቅ ትግል ውስጥ የነበሩ በኋላ ግን የሰላም አማራጭን በመቀበል ወደ ውይይት የመጡት የኢትዮጵያ አየር ኃይል የቀድሞ ባልደረባ አቶ ማስረሻ ሰጤ አንዱ ናቸው።

አቶ ማስረሻ በወቅቱ በተቋሙ ውስጥ የነበሩ ኢፍትሃዊ አሰራሮችንና የትርክት አወቃቀሮችን በመቃወም ባደረጉት ትግል ለእስር ተዳርገው እንደነበርና በ2010 ዓ.ም በለውጡ ማግስት በይቅርታ መፈታታቸውን ይናገራሉ።

ከዚያም በኋላ በተሳሳተ መንገድ የነፍጥ አማራጭን ተከትለው እንደነበር አስታውሰው÷ ከቆይታ በኋላ የትጥቅ ትግል ዘላቂ መፍትሔ እንደማያመጣ በመረዳት የሰላም ጥሪን ተቀብለው በድርድርና በሰላማዊ መንገድ ወደ ሕዝባዊ ውይይት መመለሳቸውን አስረድተዋል፡፡

አቶ ማስረሻ አሁን ላይ እየተካሄደ ስላለው ሀገራዊ ምክክር ሲያብራሩ ÷ ሒደቱ ፍትሃዊ፣ ገለልተኛና ሙሉ በሙሉ አካታች መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ ይህ የምክክር ባሕል ቀደም ብሎ ተተግብሮ ቢሆን ኖሮ የብዙ ምሁራንና የዜጎች ሕይወት ማዳን ይቻል የነበረ ሲሆን÷ አሁን ያለው መድረክ ሁሉንም የማሕበረሰብ ክፍሎች ያቀፈ በመሆኑ ለሀገራዊ መግባባት ትልቅ ተስፋን ፈጥሯል።

የጦርነትና የጥፋት ታሪክን በንግግር መተካት አስፈላጊ መሆኑን ያመላከቱት አቶ ማስረሻ÷ የትጥቅ ትግል ሕዝብን ከማንገላታትና ሀገርን ወደኋላ ከመመለስ ውጭ የፈየደው ነገር እንደሌለ ያስረዳሉ።

ባለፉት ዘመናት በሀገራችን ላይ የተንሰራፋው የልዩነትና የጨቋኝ-ተጨቋኝ ትርክት በውጭ አካላትና በውስጥ ክፍተቶች የተስፋፋ መሆኑን ጠቁመው÷ አሁን ግን የሀሳብ ልዕልናን ማረጋገጥ ብቸኛው አዋጭ መንገድ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።

በሌላ በኩል ከዚህ በፊት ያገለገሉበት የኢትዮጵያ አየር ኃይልን የአሁኑን ገጽታ በተመለከተ፣ አየር ኃይሉ ከተዳከመበት የድሮ ሁኔታ ወጥቶ አሁን ላይ በዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች፣ በፓይለቶች ክህሎትና በሙያዊ ብቃት ከፍተኛ ሪፎርም እንደተደረገበት መስክረዋል።

ተቋሙ በአሁኑ ወቅት የሀገር አለኝታና የሉአላዊነት ዘበኛ መሆኑን በኩራት ገልጸዋል።

የማህበረሰቡ፣ የምሁራንና የሚዲያው ሚና ለሀገር ግንባታ ወሳኝ መሆኑን በመጠቆም ወጣቱ ትውልድ በማህበራዊ ሚዲያ የስሜት አጀንዳዎች ሳይነዳ ምክንያታዊና ሀገራዊ አስተሳሰብን ሊያደብር እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.