በመዲናዋ ሞተር ብስክሌት ማሽከርከር ላልተወሰነ ጊዜ ተከለከለ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ከዛሬ ከመስከረም 15 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ ባለሁለት እግር ሞተር ብስክሌት በአዲስ አበባ ማሽከርከር ተክልክሏል አለ የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ እንዳስታወቀው ÷ አንዳንድ ወንጀል ፈጻሚዎች ሞተር ብስክሌትን በመጠቀም የቅሚያ እና የስርቆት ወንጀል ሲፈጽሙ ተይዘው ምርመራ እየተጣራባቸው ይገኛል።
ወንጀል ፈጻሚዎች ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር እና የተሰረቁ እቃዎችን ለማጓጓዝ ሞተር ብስክሌትን በብዛት እንደሚጠቀሙ አመልክቷል፡፡
ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች የትራፊክ ደንቡን እንደማያከብሩ በተለይ ቀይ መብራትን መጣስ፣ ሌሎች ተሽከርካሪዎችን በመግጨት ማምለጥ፣ ሄልሜት ሳያደርጉ ማሽከርከር፣ የተፋፋቀ እና ለእይታ አስቸጋሪ የሆኑ የሠሌዳ ቁጥሮችን መጠቀም በአሽከርካሪዎቹ በስፋት የሚስተዋሉ የደንብ ጥሰቶች ናቸው፡፡
ወንጀልን ለመከላከል እና በሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች የሚፈጸምን የደንብ ጥሰት ለመቆጣጠር ከዛሬ ከመስከረም 15 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ ከኮድ 4 እና ከፖሊስ ሞተር ብስክሌት ውጭ ባለ ሁለት እግር ሞተር ብስክሌት ማሽከርከር መከልከሉ ተገልጿል፡፡
የሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች እና ባለ ንብረቶች አስፈላጊውን እንዲፈጽሙ ያሳሰበው ፖሊስ ÷ ማሳሳቢያውን በሚተላለፉ ላይ ሕጋዊ ርምጃ እንደሚወስድም አስታውቋል፡፡