ሕጻናትን ከእናታቸው ጉያ የመንጠቅ የሕገ ወጡ ቡድን ህወሓት ክፉ አባዜ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይ ሕዝብን ለተደጋጋሚ ስቃይ እየዳረገ የሚገኘው ሕገ ወጡ የሕወሓት ቡድን የተከፈቱ የሰላም በሮች በመዝጋት ዛሬም የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ይገኛል፡፡
ሕገ ወጡ ቡድኑ ያለ ጦርነት መኖር የማይችል፣ የራሱን ጥቅም ከማስከበር ባለፈ ስለ ሕዝብ ሰላም እና ብሔራዊ ጥቅም ምንም አይነት ዴንታ የሌለው ጸረ ዴሞክራሲ ስብስብ ነው፡፡
ቡድኑ የጥይት ድምጽ በማጥፋት ለትግራይ ሕዝብ ተስፋ የሰጠውን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በመጣስ ክልሉን ዳግም ቀውስ ውስጥ ለመክተት ታትሮ እየሰራ ይገኛል፡፡
የቅዠት ሕልሙን ለማሳካትም በኦሮሚያ እና አማራ ክልል ከሚገኙ የጥፋት አጋሮቹ እንዲሁም ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ትብብር እየፈጠረ ይገኛል፡፡
በአንጻሩ የፌዴራል መንግሥት ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ በማቅረብና የትግራይን ሕዝብ ፍላጎት ለማሳካት በርካታ ጥረቶች አድርጓል፡፡
መንግሥት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሠረት የወደሙ መሠረተ ልማቶችንና ተቋማትን መልሶ ገንብቷል፡፡የቀድሞ ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ማሕበረሰቡ እንዲቀላቀሉም አስፈላጊውን ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ይሁን እንጅ ሕገ ወጡ ህወሓት መንግሥት በቁርጠኝነት የያዘውን የሰላም ሒደት ወደ ጎን በመተው ሕገ ወጥ ተግባሩን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ቡድኑ ለትግራይ ሕዝብ ትልቅ እፎይታን ይዞ የመጣውን የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ለጊዜ መግዣነት በመጠቀም ለሕዝቡ ምንም አይነት ክብር እንደሌለው አሳይቷል፡፡
ድንገት ያጣውን ስልጣን በድጋሚ ለማግኘትም ቡድኑ የትግራይ ክልል ወጣቶችን በአፈሳ ዘመቻ በግዳጅ በጦር ማሰልጠኛ ካምፖች እያጎራቸው ይገኛል፡፡በተለይም ሕፃናትን ከእናታቸው ጉያ በመንጠቅ የትግራይ እናቶችን ለከፋ ስነ ልቦናዊና ማህበራዊ ቀውስ እየዳረገ ይገኛል፡፡
የቡድኑ እኩይ ተግባር በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይደለም ፡፡ ቅዠት በሚመስል መልኩ ያሰበውን አቅድ ለማሳካት አልሸባብ የሽብር ቡድንን ጨምሮ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ታሪካዊ የጠላት ኃይሎች ጋር “ጽምዶ” የተሰኘ ያልተቀደሰ ጋብቻ ፈጥሯል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያን የጀመረችውን የኢኮኖሚ እድገት ጉዞ ለመግታት ሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዳይኖራት እያተራመሰ ለመኖር አቅዷል፡፡
በፍጹም ጭካኔ ሕፃናትን ከእናት ጉያ በመንጠቅና ወደ ጦር ካምፕ በማጋዝ፣ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ የሕግ ድንጋጌ የሚያስጠይቅ ሰብዓዊ ግፍ እየፈጸመ ይገኛል፡፡
በሕዝብ ሰቆቃ እና ስቃይ ላይ ሕልውናውን ለማሰንበት የሚፈልገው ይህ ሕገ ወጥ ቡድን ሰላማዊ ንግግር የማይረዳ፤ በጠብመንጃ ኃይል ወደ ስልጣን የመጣ በመሆኑ ፍላጎቶቹን ሁሉ በጠብመንጃ ማሳካት የሚፈልግ ነው።
ዕድሜውን ለማራዘም የማይፈነቅለው ድንጋይ፤ የማይምሰው ጉድጓድ የሌለው የሕወሓት ቡድን የክልሉን ሕዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ወደ ጎን በመተው የጥቂት ግለሰቦች እና ቡድኖችን ስልጣን ለማሰንበት እየተፍጨረጨረ ነው፡፡
ቡድኑ ለወታደራዊ ግዳጅ ወጣቶችን በህገ ወጥ መንገድ እያፈሰ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ይገኛል፡፡ ወጣቱን ትውልድ ለስልጣን ማራዘሚያና ለጦርነት ማገዶነት እየተጠቀመ ነው፤ ይህን የግዳጅ አፈሳ የተቃወሙ እናቶችን በማሰርም ዜጎችን ለስቃይ እየዳረገ ይገኛል፡፡
ቡድኑ ወጣቶችን ከአምልኮ ቦታዎችና ከትምህርት ቤቶች ጭምር አፍሶ እያሰለጠነ ለውጭ ኃይሎች እየሸጣቸው ሲሆን ÷ የቡድኑን ጸረ ሕዝብነት የተረዱት ወጣቶችም ክልሉን ለቅቀው እየተሰደዱ ነው፡፡
ይህንን የግዳጅ አፈሳ በመቃወም “አንገደልም፣ ውጊያ አያስፈልገንም” በሚል ለማምለጥ የሞከሩ በርካታ ወጣቶች በተለያዩ አካባቢዎች በጥይት ተደብድበው እየተገደሉ ይገኛሉ፡፡
ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን በትግራይ ክልል ሕዝብ ላይ እያካሄደ ያለውን አፈና የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ‘አፈሳ ይቁም፤ ሰላም ይስፈን’ በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
አሁን ላይም የሕገ ወጡን ህወሓት እኩይና ኋላ ቀር አስተሳሰብ የሀገር ውስጥም ሆነ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እየተገነዘበው ይገኛል፡፡
የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማትና ሀገራት የቡድኑን እኩይ ሴራ በማውገዝ የትግራይን ሕዝብ ከስቃይና መከራ ለመታደግ ከመንግሥት ጎን ሊቆሙ ይገባል፡፡