Fana: At a Speed of Life!

ምክክሩ ለዘመናት የቆዩ ልዩነቶችን በመፍታት የትውልዱን ተስፋ የሚያለመልም ነው – ተመካካሪ የሐይማኖት አባቶች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክክሩ ከተለያዩ ግጭቶችና ዘርፈ ብዙ ችግሮች የሚያሻግር አቅጣጫ በመፍጠር የትውልዱን ተስፋ የሚያለመልም ነው አሉ የሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ተሳታፊ የሐይማኖት አባቶች።

የምክክር ጉባዔው ተሳታፊ ብጹዕ አቡነ ፊሊጶስ እንዳሉት ÷ ምክክር የሰው ሕይወትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርንና ልማትን ለማስጠበቅ ወሳኝ መሣሪያ ነው።

በልዩነት ውስጥ የሌላውን ሀሳብ በአክብሮት መስማትና በጨዋነት መወያየት ለሀገር፣ ለሕዝብና ለማኅበረሰብ የጋራ ጥቅም የሚያመጣ መሆኑን ጠቁመዋል።

የትናንት ስህተቶችና መለያየቶች እንዳይደገሙ በምክክር የጋራ መግባባት መፍጠር እንደሚገባ ገልጸው ÷ ምክክር ለሀገራዊ ሰላም፣ ለሕዝብ ደህንነት፣ ለልማትና ለማኅበራዊ አብሮነት አማራጭ የሌለው መንገድ መሆኑን ተናግረዋል።

የምክክር ጉባዔው ተሳታፊ ኡስታዝ ሙክታር ጀማል በበኩላቸው ÷ ጉባዔው ኢትዮጵያ ለብዙ ዘመናት የተሸከመችውን አለመግባባትና መለያየት ለመፍታት ወሳኝ ምዕራፍ ነው ብለዋል።

የተለያዩ ሀሳቦች መኖራቸው ተፈጥሯዊ ቢሆንም ምክክሩ ለሀገር የሚጠቅሙ የጋራ ሀሳቦችን በማጠናከርና ልዩነቶችን በውይይት በማስተናገድ የጋራ አቅጣጫ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን አብራርተዋል።

የምክክሩ ሒደት ከያዝነው የአለመግባባት ታሪክ በመውጣት ለአንዲት ኢትዮጵያ የጋራ የልማትና የብልጽግና ራዕይ ለመገንባት ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው የምክክር ጉባዔው ተሳታፊ ፓስተር ተሰማ ታደሰ ናቸው።

ምክክሩ ከተለያዩ ግጭቶች እና ዘርፈ ብዙ ችግሮች የሚያሻግር አቅጣጫ በመፍጠር የትውልዱን ተስፋ የሚያበራ ሂደት መሆኑን አውስተዋል፡፡

ሁሉም ወገኖች የግልና የቡድን ጥቅምን ከማስቀደም ይልቅ የጋራ ሀገራዊ ጥቅምን ማዕከል ማድረግ እንደሚገባቸው የሐይማኖት አባቶች ጥሪ አቅርበዋል።

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.