የጸረ ሙስና ትግሉ የሕዝብና የመንግሥት ቋሚ አጀንዳ ሆኖ ሊቀጥል ይገባል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የፀረ ሙስና ትግል የሕዝብና የመንግሥት ዘላቂና ዋና አጀንዳ ሆኖ መቀጠል አለበት አሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ።
የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል ማጠቃለያ መድረክ “የፀረ ሙስና ትግል ትናንት፣ ዛሬና ነገ”በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ነው፡፡
ም/አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ዛሬ የምናከብረው የጸረ ሙስና ትግል ያለፈውን ለመዘከር ብቻ ሳይሆን፣ ያለንበትን ለመገምገምና ወደፊት የምንመራበትን አቅጣጫ ለመወሰን የሚያስችለን ነው።
በሀገራዊ ምክክሩ ዋና ዋና መወያያ ነጥቦች መካከል ሙስና እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች በግንባር ቀደምትነት የተቀመጠ አጀንዳ መሆኑን አንስተው ÷ የፀረሙስና ትግሉ የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን የመላው ህዝብ የጋራ ሀገራዊ ህልውና ጉዳይ መሆኑን ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
እነዚህ ሶስት መሰረቶች የፀረ-ሙስና ትግሉ የማዕዘን ድንጋዮች ሆነው አሁንም ያገለግላሉ ሲሉ አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት መንግሥት ሙስናን ለመታገል ዘመናዊ እና መዋቅራዊ የሪፎርም ስራዎችን በስፋት እየተገበረ እንደሚገኝ ጠቁመው÷ በተለይም ሀገራዊ የጥቆማ መቀበያ ሥርዓት፣ የዜጎችን ድምፅ ያለስጋት እንዲሰማ አድርጓል ብለዋል።
ዲጂታል የሀብት ማሳወቂያ እና ማስመዘገቢያ ሥርዓት ደግሞ የመንግሥት ተቋማት አመራር እና ሰራተኞች ሀብት ለህዝብ ግልጽ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡
በመሶብ የአንድ መስኮት አገልግሎትና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤአይ) የተደገፉ አሰራሮች ሌብነትን በቴክኖሎጂ አቅም የሚያጋልጡ አዲስ የትግል ምዕራፎች መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡
ሙስና የገንዘብ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሥነ-ምግባር፣ የሞራል፣ የአስተዳደር፣ የፍትሕ፣ የልማት፣ የሀገር እና የትውልድ ግንባታ ጉዳይ በመሆኑ ሁሌም ቋሚ የሕዝብና የመንግሥት አጀንዳ ሆኖ ሊቀጥል እንደሚገባም ወይዘሮ ሎሚ አስገንዝበዋል።