Fana: At a Speed of Life!

ባንዳ የሚሞተው ለሆዱ ነው – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ በተለየ ወታደራዊ ጥበብ በፍጥነት ፈጣን ምላሽ ሰጪና አስቀድሞ ስጋቶችን መከላከል የሚችል የመከላከያ ዋነኛ መቺ ሀይል ነው አሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የ2018 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም ውይይት ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው ስለወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ለሠራዊቱ አመራሮች የስራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡
ፊልድ ማርሻሉ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ በተለየ ወታደራዊ ጥበብ በፍጥነት ፈጣን ምላሽ ሰጪና አስቀድሞ ስጋቶችን መከላከል የሚችል የመከላከያ ዋነኛ ስትራቴጂካዊ መቺ ሃይል ነው ብለዋል።
አክለውም ኢትዮጵያ የሥርዓት ለውጥ አድርጋ ገና ሳትረጋጋ ባንዳዎች ባደረሱባት ጥቃት ሀገር በተፈተነችበት ወቅት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ሠራዊት የተደቀነውን አደጋን በመቀልበስ ረገድ ከባድ የተጋድሎ ትግል አድርጓል ነው ያሉት።
በዚህም ምክንያት “የውጊያ ማርሽ ቀያሪ የምድር ድሮን” የሚል ስያሜ የተሰጠው ልዩ ሀይል መሆኑን በማብራራት ይህ ዕዝ አስካሁን ለሀገር ለከፈለው ዋጋ ኢትዮጵያ እንደምታከብረውና ነገም ይህንኑ ልዩ ብቃቱን ይዞ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል፡፡
ሠራዊቱ መስዋዕትነት የከፈለውና እየከፈለ የሚገኘው ሀገርን ለማሻገር በመሆኑ ሀገርን ከውጭ ጠላት ከመከላከል ባለፈ፣ የሀገር ውስጥ ሰላምን በማጽናት ሀገራዊ ህልውናችን ተጠብቆ ዕድገት እንዲቀጥል የሚያስችል፣ የሀገር አንድነትና የህግ የበላይነት እንዲከበር የዜጎች ክብር መገለጫ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።
ሻዕቢያ ከጅምሩ ኢትዮጵያን ከባሕር በር ለማራቅ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር ፅምዶ ፈጥሮ ኢትዮጵያ ላይ ደባ የሰራ ሃይል መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
ሕገ ወጡ ህወሓትም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ የሸጠና ለ27 ዓመታት ስልጣን ይዞ ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታጣ አጠንክሮ የሰራ ቅጥረኛ የገዛ ሀገሩን ሠራዊት ያጠቃ የክህደት ሃይል ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በሕወሃት ክህደት የተፈተነች ነገር ግን ፀንታ የቆመች የልዩ ዘመቻ ሠራዊት መሰል ጠንካራ አርበኛ ልጆች ያሏት ሀገር ስለሆነች ጉዞዋን ቀጥላለች ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ፅንፈኞቹን የጥፋት ሃይሎች በባዕዳን ስትራቴጂ ሥር ተሰልፈው ኢትዮጵያን የማዳከምና የማፍረስ ፅምዶ የተባለ ጥምረት ቀርፀው ሕዝባችንን ለስቃይና መከራ በመዳረግ ደካማ ኢትዮጵያን ለማየት ጓጉተው ቢሠሩም ይህ ፍላጎታቸው መቼም ሊሳካ እንደማይችል አሳይተናቸዋል ነው ያሉት።
ወያኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ በመከፋፈል እርስ በርሱ እንዳይተማመን ያደርግ እንደነበረ አውስተው÷ የትግራይን ህዝብ ደግሞ የኢትዮጵያ ልጆች እየመጡብህና እየከበቡህ ነው እያለ ከወንድም የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በጠላትነት እንዲተያይ ሲሰራ የኖረ እኩይ ፖለቲካ አራማጅ ፀረ ሀገር ሃይል ነው ብለዋል።
ዛሬ ላይ ያ ሁሉ ሴራ ከሽፎ የትግራይ ህዝብን ጨምሮ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ የዚህን መሰሪ ቡድን መጥፎ ተግባር በመረዳቱ ወያኔ ከህዝብ ተነጥሎ መንጠልጠያ ሲያጣ የቀድሞ ጠላቶቹን ሸኔንና ፅንፈኛ ፋኖን አቅፎ ሻዕቢያን ደግሞ አዝሎ የትላንት ክህደቱን በአደባባይ እየደገመው ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ አባላት እነዚህ የጥፋት መልዕክተኞች በኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ የደቀኑትን ጥፋት በማምከን የጥፋት እግራቸውን በመስበር እብሪታቸውን ማስተንፈስ እንዳለባቸው አሳስበዋል ።
በተለይ የሕገ ወጡ ህወሓትንና የጽንፈኞችን የተላላኪነት ሚና መስባበር የሻዕቢያንና የሻዕቢያ ነብስ አባቶችን ተስፋ ማጨለም እንደሆነ በማስረዳት ለሀገር ውስጥ ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ በጀመረችው እድገትና ብልፅግና ወደፊት ትቀጥላለች፤ የታሪካዊ ጠላቶቿ ህልም አይሳካም የልዩ ዘመቻዎች ጦር ከኢትዮጵያ አያቶች የተቀዳ አርበኛ ነው ማለታቸውን የመከላከያ ሰራዊት ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡
የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ በአሁኑ ወቅት በትጥቅም በሰው ሀይል ግንባታ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን በማስታወስ ለሰፈር ባንዳዎች ብቻ ሳይሆን በየትኛውም አቅጣጫ በሀገር ላይ ለሚቃጣ ጥቃት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆን እንደዳለበት አሳስበዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.