የአረንጓዴ ዐሻራ ለማንጎ ምርታማነት
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አፍላቂነት የተጀመረው የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአካባቢ ጥበቃን ከምግብ ዋስትና እና ከኢኮኖሚ እድገት ጋር አስተሳስሮ በመምራት ረገድ ታሪካዊ ስኬት እያስመዘገበ ይገኛል።
ይህ መርሐ ግብር የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባሻገር፣ ለምግብነትና ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚውሉ ተክሎችን በስፋት በመትከል ረገድ ትልቅ ምዕራፍ ከፍቷል።
ከእነዚህም መካከል የማንጎ ልማት አንዱና ዋናው የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ በመተግበር ላይ ይገኛል።
የአረንጓዴ ዐሻራ በተለይም በሁለተኛው ምዕራፉ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ለሚያስችሉ አትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች ልዩ ትኩረት ሰጥቷል።
በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የተከናወኑ የተፋሰስ ልማቶችና የችግኝ ተከላዎች፣ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል፣ የከርሰ ምድር ውሃን በማበልጸግና የስነ-ምህዳር መረጋጋትን በመፍጠር ለማንጎ ልማት ተስማሚ የሆነ የአየር ንብረትና ለም አፈር እንዲፈጠር አድርገዋል።
በየዓመቱ ከሚተከሉት በቢሊየን የሚቆጠሩ ችግኞች መካከል የተሻሻሉ የማንጎ ችግኞች በመካተታቸው፣ የሀገሪቱን የፍራፍሬ ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ አሳድገውታል።
የማንጎ ችግኝ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በስፋት መተከሉ ለአነስተኛ አርሶ አደሮች ቀጥተኛ የኢኮኖሚ ጥቅም በማስገኘት ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
አርሶ አደሮች የተሻሻሉ የማንጎ ዝርያዎችን በማልማት ጥራት ያለው ምርት ለገበያ በማቅረብ ገቢያቸውን ማሳደግ የቻሉ ሲሆን÷ ይህም የቤተሰቦቻቸውን የምግብና ሥርዓተ ምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
በተጨማሪም፣ የችግኝ ማዘጋጃ ጣቢያዎችን በማቋቋም፣ በእንክብካቤ፣ በምርት ስብሰባ፣ በማሸግና በገበያ ሰንሰለት ውስጥ ለበርካታ ሴቶችና ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።
በሌላ በኩል፣ የመርሐ ግብሩ ስኬት የኢትዮጵያን የፍራፍሬ ኤክስፖርት ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ አሻሽሎታል።
ጥራታቸው የተጠበቀና በተፈጥሯዊ መንገድ የበቀሉ የማንጎ ምርቶች ለአገር ውስጥ ፍጆታ ከመዋላቸው ባሻገር ለጅቡቲ እና ለሌሎች የጎረቤት ሀገራት፣ ለመካከለኛው ምስራቅ እንዲሁም ለአውሮፓ ገበያዎች መላክ ተጀምሯል።
ይህም ሀገሪቱ ከግብርና ምርቶች የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግና የማንጎ ኤክስፖርት ዘርፉን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ነው።
በአብረሃም አበራ