በአፋር ክልል ከ450 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው የጤና በጎ ፈቃድ አገልግሎት
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፋር ክልል ከ450 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የጤና በጎ ፈቃድ አገልግሎት በዛሬው ዕለት ተጀምሯል።
በተያዘው ክረምት ከፍለው መታከም የማይችሉ ዜጎችን በጤና በጎ ፈቃድ ለማከም የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ጤና ቢሮ ገልጿል።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የዓይን እና የጆሮ ሕክምና፣ የደም ግፊት፣ የስኳር በሽታ፣ የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር እንዲሁም የኤችአይቪ እና የሄፓታይተስ ቢ ምርመራ ይደረጋል።
የዱብቲ ጠቅላላ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር መሐመድ የሱፍ በበኩላቸው÷ አገልግሎቱ በከተማው በተቋቋሙ ቋሚ ጣቢያዎች እና በተንቀሳቃሽ የሕክምና ቡድኖች አማካኝነት ለተጠቃሚዎች እየቀረበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በሆስፒታሉ ብቻ 85 ሺህ ሰዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ በርካታ የሕብረተሰብ ክፍሎች ነጻ የሕክምና አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑ የዱብቲ ከተማ ነዋሪዎች ÷ የነጻ ምርመራ እና ሕክምና አገልግሎቱ የጤና ሁኔታቸውን አውቀው አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ማህበራዊ ትስስርን ከማጠናከር ባለፈ የሕብረተሰቡን ጤና በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ማለታቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።