Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል ከወርቅና ሌሎች ማዕድናት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጋምቤላ ክልል ከወርቅና ሌሎች ማዕድናት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ፡፡
የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት 6ኛ የምርጫ ጊዜ 5ኛ የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባዔ እየተካሄደ ነው፡፡
ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ በክልሉ የሕዝቦችን አብሮነትና አንድነት በማጎልበት ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት በቁርጠኝነት እየተሰራ ይገኛል፡፡
በግብርና ዘርፍ አበረታች አፈጻጸም መመዝገቡን ጠቁመው ÷ በ2017/18 የምርት ዘመን 172 ሺህ 239 ሔክታር መሬት በመኸር እርሻ በሰብል ለመሸፈን ታቅዶ 190 ሺህ 631 ሔክታር በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል።
በዚህም 6 ሚሊየን 223 ሺህ 184 ኩንታል ምርት መሰብሰብ መቻሉን ነው ርዕሰ መስተዳድሯ ያስረዱት፡፡
በዓመቱ ከ5 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል ያሉት ወ/ሮ አለሚቱ ÷ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ2 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩል ከወርቅና ሌሎች ማዕድናት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በዚህም 6 ሺህ ኪሎ ግራም የተጣራ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ለማስገባት ታቅዶ ከ7 ሺህ 98 ኪሎ ግራም በላይ የተጣራ ወርቅ ማስገባት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
አፈጻጸሙ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ1 ሺህ 669 ኪሎ ግራም ብልጫ እንዳለው አብራርተዋል፡፡
በቀጣይ የተገኙ ውጤቶችን በማስቀጠልና ያሉ ክፍተቶችን በማረም ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል ማለታቸውንም የክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት መረጃ አመልክቷል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.