Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና በተላውጦ ውስጥ ያለው ዓለም

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በከፍተኛ ተላውጦና መናወጥ ውስጥ በምትገኘው ዓለማችን የኃይል ሚዛን እየተቀያየረ፣ አዳዲስ ኃያላን እየተዋለዱ፤ አይጠበቄ ጦርነቶችና አጋርነቶችም እየታዩ ነው።

በዚህ ተለዋዋጭ ጂኦፖለቲካ ውስጥ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ለማንም ያልወገነ ገለልተኛ የውጭ ግንኙነት መንገድን እየተከተለች ትገኛለች።

በፈረንጆቹ በ1991 የቀዝቃዛው ጦርነትን ማብቂያ ተከትሎ የተፈጠረው የዓለም ሥርዓት በአሜሪካ መሪነት የተመሠረተ የአንድ ኃያል የበላይነት፣ የነጻ ገበያ ካፒታሊዝም መስፋፋትና የሉላዊነት ማዕበል የገነነበት ነበር።

አሁን ላይ የዓለም የኃይል አሰላለፍ ተቀይሯል፤ ከአንድ ወገን የበላይነት ወጥቶ አዳዲስ ኃያላን እየመጡ ነው።

ዓለም ከምዕራባውያን የበላይነት ወጥቶ ቻይናና ሕንድን የመሳሰሉ አዳዲስ በኢኮኖሚና በፖለቲካው መስክ ጡንቻቸውን ያፈረጠሙ ሀገራት እየተፈጠሩበት ነው።

በዚህም የዓለም ኃይል በአንድ ሀገር ቁጥጥር ብቻ ሳይሆን በበርካታ ሀገራት መካከል የተከፋፈለ ሲሆን፤ እንደ አሜሪካ፣ ምዕራባውያን ሀገራት፣ ቻይና፣ ኢራን፣ እስራኤል እና ሩሲያን በመሳሰሉ ሀገራት መካከል ከፍተኛ የጂኦፖለቲካ ሽኩቻ እየተስተዋለ ይገኛል፡፡

በተለዋዋጩ የዓለም ጂኦፖለቲካ ውስጥ ኢትዮጵያም ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ለማንም ያልወገነ ገለልተኛ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲን ብቸኛ አማራጯ አድርጋለች፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት አቅጣጫ ሲያብራሩ፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ለውጦች መካከል ንቁ፣ ተለዋዋጭና አጀንዳ ፈጣሪ የሆነ ዲፕሎማሲን እየተከተለች መሆኑን አመላክተዋል።

ዓለም በፍጥነት በምትለዋወጥበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ከለውጦቹ ራሷን አግልላ የምትቆይ ሳይሆን፣ በንቃት የምትሳተፍና ጥቅሟን በግልጽ የምታስከብር እንድትሆን የሚያስችላትን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እየተከተለች መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በጥቂት ሀገራት ላይ ብቻ የተመሰረተ ግንኙነት ከመከተል ይልቅ፣ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ዘላቂና ተጨባጭ የጋራ ጥቅም ያላቸውን ሰፋፊ ግንኙነቶች እየመሰረተች እንደምትገኝ ጠቁመዋል፡፡

የሀገሪቱ የውጭ ግንኙነት አሰላለፍ የሚበየነው ጠላትና ወዳጅ በመፍጠር ሳይሆን በብሔራዊ ጥቅም ስሌት ነው።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ተቋማትና መድረኮች ላይ ፍላጎቷን በቆራጥነት የገለፀች ሲሆን÷ ከአጀንዳ ተቀባይነት ወደ አጀንዳ ፈጣሪነት መሸጋገርም ችላለች፡፡

በዚህም የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ከተለዋዋጭ የዓለም ሁኔታ ጋር በመጣጣምና በሌሎች ሀገራት ከተወሰኑ ገደቦች ነፃ በመሆን የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም እያስከበረ ይገኛል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.