ቻይና የሰጠችው እውቅና
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ባለፈጣን አዳጊ ኢኮኖሚ ሀገራት መካከል ናት አሉ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይ።
የኢትዮጵያና የቻይናን ዘላቂና ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ወደ ላቀ የንግድና ኢኮኖሚ ትስስር የሚያሸጋግረው “ወደ ቻይና ኤክስፖርት” መድረክ ተካሂዷል፡፡
አምባሳደሩ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ተለዋዋጭ የገበያ ሁኔታ ያላት እና ከፍተኛ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሀገር መሆኗን ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአፍሪካ ካሉ ግዙፍ ኢኮኖሚዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ፥ ቻይና ለአፍሪካ ሀገራት ከምትሰጠው ከታሪፍ ነፃ የንግድ እድል ተጠቃሚ ሀገር መሆኗን በመጠቀስ፤ የሀገራቱ የንግድ ግንኙነት እየተጠናከረ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
ይህ የንግድ ትብብር የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማስቻሉንም ነው የተናገሩት።
ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማሳደግ እንዲሁም የወጭ ምርቶችን በዓለም አቀፍ ገበያዎች ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግ ለምታደርገው ጥረት ሀገራቸው ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ቻይና የብሪክስ አባል ሀገራት መሆናቸውን በመጥቀስ በዓለም አቀፍ ንግድና ኢኮኖሚ ዙሪያ በትብብር መስራታቸውን ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡
ለኢትዮጵያ ትልቅ የንግድ አጋር ስትሆን በ12 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በሚገነባው የቢሾፍቱ የአውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ የግንባታ ውሎችን ከሚወስዱ ሀገራት መካከል ቻይና አንዷ መሆኗን ቢዝነስ አፍሪካ ዘግቧል፡፡
እንደ ቤጂንግ አርባን ኮንስትራክሽን ግሩፕ፣ ቻይና ኮሚዩኒኬሽንስ ኮንስትራክሽን ኩባንያ፣ የቻይና ሮድ ኤንድ ብሪጅ ኮርፖሬሽን እና ቻይና ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ የሚገኙ የቻይና የግንባታ ዘርፍ ኩባንያዎች ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ እና ቻይና የንግድ ግንኙነት እየተጠናከረ የመጣ ሲሆን፥ ከቀናት በፊት ኢትዮጵያና ቻይና ከ340 ሚሊየን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው 33 የንግድ ለንግድ ግብይት ስምምነቶችን ተፈራርመዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ