Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የጤና ኢኮኖሚ መዳረሻ ለመሆን እየሠራች ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የአፍሪካ የጤና ኢኮኖሚ መዳረሻና ማዕከል ለመሆን በትኩረት እየሠራች ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።

13ኛው የምስራቅ አፍሪካ የጤና ፌዴሬሽን ኮንፈረንስና ዓለም አቀፍ የጤና ኤግዚቢሽን በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ተጀምሯል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመክፈቻው ላይ ባደረጉት ንግግር ሉዓላዊነትን ማስከበር ማለት የዜጎችን ጤና ከመጠበቅ ጋር በቀጥታ እንደሚያያዝ አስገንዝበዋል።

ሀገራዊ ሉዓላዊነትን በተሟላ ሁኔታ ማረጋገጥ የሚቻለው መድኃኒቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት ሲቻል፣ የጤና ባለሙያዎችን በበቂ ሁኔታ ማሰልጠንና ማቆየት ሲቻል ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የአፍሪካን ፍላጎት በራስ አቅም ማሳካትና ወረርሽኞችን መቋቋም እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

እንደ ሀገር ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሚያጋጥሙ የጤና ስጋቶችና ችግሮች መትረፍ ብቻ ሳይሆን፤ በየጊዜው የሚያድግና የሚበለፅግ የጤና ሥርዓት መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የአፍሪካ ጤና ፌዴሬሽን አህጉራዊ ዋና መሥሪያ ቤት በአዲስ አበባ እንዲቋቋም ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ገልጸው፤ ይህም ኢትዮጵያን የአፍሪካ የጤና ኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት የሚያፋጥን ነው ብለዋል።

ይህንን ዓላማ እውን ለማድረግ ከፌዴሬሽኑና አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር መዋቅራዊ ውይይት ለማድረግ፣ የሕግ ማዕቀፎችን ለማዘጋጀትና ተግባራዊ ርምጃዎችን ለመውሰድ መንግሥት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ የፋርማሲዩቲካል፣ የምርመራ፣ የሕክምና መሣሪያዎችና አስፈላጊ የጤና ምርቶች የሀገር ውስጥ ማምረቻዎችን ለማስፋፋትና የዘርፉን ዕድገት በመንግሥትና በግል ዘርፍ ትብብር ለማጠናከር እየሠራች መሆኑን ገልጸዋል።

ቀጣናዊ የጤና ዘርፍ ልማትን ዕውን ለማድረግ ታካሚዎችንም ሆነ የሕክምና መሣሪያዎችን ሙሉ በሙሉ ከውጭ በማስገባት ላይ የተደገፈ አሠራርን መቀየር እንደሚገባ አሳስበዋል።

በምትኩ ሕዝቡን በቅርበት የሚንከባከብና አስፈላጊ የሕክምና ግብዓቶችን በራስ አቅም የሚያመርት የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን እውን ማድረግ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

በለይኩን ዓለም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.