Fana: At a Speed of Life!

አለመግባባት የወለደው ምክክር

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ ምክክሩን የወለደው ችግር ነው፤ አለመግባባት ነው ለመግባባት ወንበር አስቦ ያስቀመጠን። ልዩነት ራሱ ንግግርን ወለደ፤ ጭቅጭቅ ጠረጴዛን አዘጋጀ። የዚህ መንገድ ሥሙ ስልጡንነት ይባላል።

ኢትዮጵያ ሁለት ገጽ አላት። አንደኛው ገጿ ላይ ክብር፣ ጀግንነትና ነጻነት ይነበባል። ሌላኛው ገጿ ደግሞ ጦርነተት፣ መቃቃርና ረሃብ ተጽፎበታል።

ኢትዮጵያ ጠላቶቿን ደጋግማ አሳፍራ መልሳለች። በዓድዋ ተራሮች የቅኝ ገዥን ጦር ድል በማድረግ ለመላው ጥቁር ሕዝብ የነጻነት ፍኖት ገላጭ ሆነች።

በተደጋጋሚ የውጭ ወረራዎችን በመቋቋም ሉዓላዊነትና ነጻነቷን አስጠብቃለች። ይህ ታሪክ ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያውያንን ደረት የሚያስነፋ ኩራት ነው።

በሌላ በኩል ግን ኢትዮጵያ የራሷ ልጆች እርስ በርስ ተጋጭተው ተቆራቁሰው ያለፉባቸው ዘመናት ብዙ ናቸው። ያለመደማመጥና ያለመወያየት ክፉ ልማድ ደጋግሞ ወደ ግጭት፣ ወደ ረሃብ፣ ወደ መፈናቀል መርቶናል።

ለጠላት ያበረ ጀግንነታችን ወንበር ስቦ ለመቀመጥ ከእህት ወንድማችን ጋር ለመምከር አልሆነንም። የውጭ ጠላትን የረታንበት ብርታት፣ የውስጥ አለመግባባትን ለመፍታት ሰንፎብናል።

ያለፉት አያሌ ዓመታት ይህን እውነታ በግልጽ አሳይተውናል። አለመደማመጥ ዋጋ እንዳስከፈለን ድብዝዝ ትዝታዎቻችን ይመሰክራሉ፤ የፖለቲካ ልዩነት ወደ ጦር ሜዳ የተቀየረባቸው አጋጣሚዎች፣ በህዝቦች መካከል አለመተማመን ወደ ግጭት ያመራባቸው ወቅቶች፣ ንግግር ባልተካሄደበት ልዩነት የተፈጠረ መራራቅ እነዚህ ሁሉ የአንድ እውነታ ማሳያዎች ናቸው።

ኢትዮጵያውያን መነጋገርን ችላ ባልንበት መጠን ከመፍትሄው ርቀናል፣ ያለመግባባት ክፉ ውጤት ተጋሪዎችም ሆነናል።

ሀገራዊ ምክክሩ የተወለደው ከዚህ ሁሉ ውስብስብ መክል ነው። እንደ ቀዳሚዎቹ የፖለቲካ አካሄዶች ልዩነትን በኃይል ለመፍታት የሚሞክር ሳይሆን፣ ልዩነትን በጠረጴዛ ዙሪያ ለማስተናገድ የተቀየሰ አዲስ መንገድ ነው።

ይህ ሂደት የሚለየው በአንድ ነገር ነው። ችግሩ ራሱ መፍትሄውን ጠቁሟል። ልክ እንደ ቁስል መጀመሪያ የሚያሳምም፣ ነገር ግን ፈውስ እንዲፈለግ የሚያደርግ፣ የኢትዮጵያ የተደራረቡ ቀውሶች ራሳቸው ወደ መደማመጥ የሚያደርስ በር ከፍተዋል።

ኢትዮጵያውያን ብንጣላም፣ ብንኳረፍም፣ ከዚያ ባሻገር ያለን ትስስር ግን ከሁሉ በላጭ ነው። ኢትዮጵያውያን በአንድ ቤተሰብ እንመሰላለን። ታሪክም፣ እምነትም፣ እውነትም ተጋሪዎች ነን።

ባለመደማመጣችን የገጠሙን ቁርሾዎች ጥል ወልደዋል። መጣላትና መቋሰል የቤተሰብነትን ትስስር አያፈርሱም።

ልዩነታችን የክፍፍል ምንጭ ሳይሆን የውይይት ምንጭ ሊሆን ይችላል። መቋሰላችን ከዝምድናችን የሚነጥለን አይደለም፤ ይልቁንም የዝምድናችን አካል ነው።

የሀገራዊ ምክክሩ ሁሉን ችግሮቻችን ይፈታል ባይባልም ለነጋችን ግን መሰረት ይጥላል። በዘመናት የተከማቸ ችግራችን፣ ያልተነገረ ቁጭታችን፣ እና ያልተደመጠ ህመማችን የተደመጠበት ሁነት ነው።

ኢትዮጵያ ጠላቶቿን ድል በማድረግ የተካነችውን ያህል ብርታት፣ ራሷን ከራሷ ጋር በማስታረቅ ስራ ላይ ልታውለው ይገባል። ይህ ደግሞ ከጦር ሜዳ ብርታት የተለየ፣ ነገር ግን የማያንስ፣ የመደማመጥና የመቻቻል ብርታት ይጠይቃል።

አለመግባባት ወንበር አዘጋጅቶልናል። ወንበሩ ላይ ተቀምጠን የምንሰራው ስራ ግን የኛ ፈንታ ነው።

በአፈወርቅ እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.