ተስፋን አብሳሪዎቹ ጎቤና ሺኖዬ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጎቤ እና ሺኖዬ የክረምቱ ጨለማ ተጠናቅቆ ብርሃን የሚታወጅበት ባህላዊ ሥርዓት ነው።
አሮጌው ዓመት አልፎ አዲሱ ዓመት ሲመጣ፣ ተፈጥሮ፣ እፅዋትና የአየር ሁኔታም አዲስ መልክ ይይዛሉ።
የክረምቱ ዝናብ አልፎ መሬቱ በአበቦችና በለመለሙ ተክሎች ይሸፈናል። ወጣቶችም ከክረምቱ የሥራ ጊዜ ዕረፍት አግኝተው፣ ተፈጥሮ ይዞት የመጣውን አዲስ ተስፋ ይቀበላሉ።
በዚህም አዲስ ተስፋ፣ ደስታና ብሩህ ፊት ይዘው ወደ ሜዳ በመውጣት በዓል ያከብራሉ። ይህንን ባህላዊ በዓል ጎቤ እና ሺኖዬ ብለው ይጠሩታል።
ጎቤ እና ሺኖዬ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የሚከበሩ ሲሆን፤ አከባበራቸውም እንደየአካባቢው በተለያየ መልኩ ይከናወናል።
በኦሮሞ ባህል ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣው ጎቤ እና ሺኖዬ፣ በተለይም በበልግ ወቅት ወጣቶች ባህላዊ ልብስ በመልበስ፣ በባህላዊ ዘፈንና ጨዋታ በመሳተፍ ደስታቸውንና መልካም ምኞታቸውን የሚገልጹበት ሥርዓት ነው።
እነዚህ ባህላዊ ጨዋታዎች የኦሮሞን ታሪክና ማንነት ለአዲሱ ትውልድ ከማስተላለፍ ባለፈ፤ እየተረሳ የመጣውን ባህል ለመመለስ፣ ማኅበራዊ ትስስርን ለማጠናከርና የኦሮሚያን የቱሪዝም ማራኪነት ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና አላቸው።
ወጣት ወንዶችና ሴቶች የወረሃ መስከረም መጥባትን በምስጋና፣ በልዩ ልዩ ዜማዎችና ዘፈኖች ይቀበላሉ።
ሴቶች ወረሃ መስከረምን በሺኖዬ፣ ወንዶች ደግሞ በጎቤ በመግለጽ፣ ለፈጣሪና ለተፈጥሮ ያላቸውን ምስጋና፣ ተስፋና ደስታ ያሳያሉ።
የጎቤ ሥርዓት ከክረምቱ ዝናብ ወደ ብራ ወቅት የሚደረገውን ሽግግር የሚያመለክት ሲሆን፣ ይህም ከክረምት ወደ በጋ ለሚደረገው ሽግግር ፈጣሪን የሚያመሰግኑበት ሥርዓት ነው።
ወረሃ መስከረም ተስፋ፣ እርቅ፣ ብልጽግናና ደስታ ነው። ኦሮሞዎችም በፍልስፍናቸው ወሩን “ቦቃ” ብለው የሚያወድሱት ለዚህ ነው።
ወጣት ወንዶች በጎቤ ጀግንነትን፣ ልማትንና ሰላምን ያወድሳሉ፤ በጎቤም በጀግንነታቸው ይመካሉ።
ጎቤ እና ሺኖዬ ከችግር ወደ ምቾት፣ ከመከራ ወደ ሰላም መሸጋገርን፣ ችግሮችን በጽናት ማለፍንና አዲስ ምዕራፍ መከፈቱን የሚያበስሩበት ባህላዊ ሥርዓቶች ናቸው።
ሴቶችም እርጥብ ሣር በእጃቸው ይዘው፣ ሰላም፣ ደስታ፣ ብልጽግናና መረጋጋት በየቤቱና በየመንደሩ እንዲሰፍን፣ የዘመተውም በሰላም እንዲመለስ፣ የግጭት ጨለማ አልፎ የሰላም ብርሃን እንዲበራ በዘፈን ያውጃሉ።
ይህም የኦሮሞ ሕዝብ ሰላማዊ ትውልድን እንዲወድ፣ አንድነትን እንዲመኝና ለሚመጣው ትውልድ መልካም አሻራ እንዲተው የሚያበረታታ ነው።
የጎቤም ሆነ የሺኖዬ ሥርዓት በትውልድና በዘር ቀጣይነት ላይ ያተኩራል። ወጣት ወንዶችና ሴቶችም ያለፈውን ትውልድ ከሚመጣው ትውልድ የሚያገናኙ ድልድይ ሆነው ያገለግላሉ።
ጎቤ እና ሺኖዬ/አሴሳ አዲሱን ትውልድ ወደ ጥንታዊ ባህሉና ወጉ በመመለስ የሚጫወቱት ሚና ቀላል አይደለም።
ጎቤ እና ሺኖዬ ትዳር የመሠረቱ ሰዎች የማይሳተፉበት፤ ወጣቶች ብቻ ይሳተፉበታል።
የወጣቶችንና የሴቶችን መብት ከማክበር እስከ በሰውና በተፈጥሮ መካከል ያለውን ትስስር መግለጽ እሴቶች ናቸው። ባህላዊ ሥርዓቱ አሁንም በመጠናከር፣ በመታደስና በመጎልበት ቀጥሏል።
በአቤል ነዋይ