Fana: At a Speed of Life!

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ግዳጁን በአስተማማኝ ብቃት በመወጣት የሕዝብ ልጅ መሆኑን በተግባር እያስመሰከረ ነው – ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የሚሰጠውን ግዳጅ በአስተማማኝ ብቃት በመወጣት የሕዝብ ልጅ መሆኑን በተግባር እያስመሰከረ መሆኑን የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ።

የብላቴ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ዋና ማሠልጠኛ ማዕከል 45ኛ ዙር የጽናት ኮርስ ኮማንዶዎችን አስመርቋል።

በመርሐ ግብሩ የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል አበባው ታደሰ እና የመከላከያ ሠራዊት ጄኔራል መኮንኖች ተገኝተዋል።

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ የተሰጠውን ተልዕኮ በላቀ ውጤት እየፈጸመ ነው።

በዚህም በተለያዩ የውጊያ አውዶች የሚሰጡትን ግዳጆች በብቃት በመወጣት የምድር ድሮንነቱን በተግባር እያስመሰከረ የሚገኝ የሕዝብ ልጅ መሆኑን ገልጸዋል።

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ማሠልጠኛም የማሠልጠን አቅሙን በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ ሰላምና ደኅንነት የሚያስጠብቁ በርካታ የኮማንዶ ሠራዊት እያፈራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

45ኛ ዙር ሰልጣኞችም ውስብስብና ጽናትን የሚጠይቁ የንድፈ ሐሳብና የተግባር ወታደራዊ ሳይንስና ጥበብን በመቅሰም፣ የሠራዊቱን ወትሮ ዝግጁነት በላቀ ብቃት የመፈጸም አቅም በሚያጎለብት መልኩ ለምርቃት መብቃታቸውን አንስተዋል።

በቀጣይም ሠራዊቱ የሚሰጠውን ግዳጅ በብቃት በመወጣት የሀገርንና የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የብላቴ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ማሠልጠኛ ማዕከል ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ቦጃ አጋ በበኩላቸው፤ 45ኛው ዙር የጽናት ኮርስ ተመራቂዎች ለተለያዩ የውጊያ አውዶች የተጠናከረ አቅም መገንባታቸውን ተናግረዋል።

ሰልጣኞች በቆይታቸው እልህ አስጨራሽ ሥልጠና ወስደው ለምርቃት በቅተዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ተመራቂዎች በተለያዩ የውጊያ አውዶች ድል መቀዳጀት የሚያስችላቸውን አቅም መገንባት መቻላቸውን ተናግረዋል።

ሰልጣኞች በጠንካራ ሥነ ምግባር ዘመኑን የዋጀ ሥልጠና ተከታትለዋል ያሉት ዋና አዛዡ፤ ማሠልጠኛ ማዕከሉ በየጊዜው ብቁ ሠራዊት የማፍራት ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ሰልጣኞች ውስብስብ የውጊያ አውዶችንና ግዳጆችን በአስተማማኝ ሁኔታ የመፈጸም አቅም በመላበስ፣ በወታደራዊ ሥነ ምግባር እንዲሁም በአካል ብቃት ብቁ ሆነው መውጣታቸውንም ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.