Fana: At a Speed of Life!

የቀይ ባህርን ደህንነት ስጋትና የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሁቲ አማፂያን በቁልፉ መተላለፊያ የባብ ኤል መንዳብ መስመር በሚፈፅሙት ተደጋጋሚ ጥቃት የቀይ ባህር ደህንነት ስጋት ውስጥ እየወደቀ ይገኛል፡፡

የሁቲ አማፂያን ጥቃት፣ የባህር ላይ ውንብድና እና የጂኦፖለቲካ ፉክክሮች የቀይ ባህር የንግድ እንቅስቀሴ እና ደህንነትን በእጅጉ እየፈተኑት ይገኛሉ፡፡

ቀደም ሲል የሁቲ አማፂያን በባብ ኢል መንዳብ እና በቀይ ባህር የባህር ጠረፍ መስመር በእስራኤል፣ በአሜሪካ እና በአጋሮቻቸው የንግድ እንዲሁም የጦር መርከቦች ላይ ተደጋጋሚ የሚሳኤልና የድሮን ጥቃቶችን ሲፈፅሙ ቆይተዋል፡፡

ቡድኑ በፈፀማቸው ጥቃቶች የበርካታ መርከበኞችን ሕይዎት ከመቅጠፍ ባለፈ የዓለምን የንግድ እንቅስቃሴ አደጋ ላይ ጥለው ቆይተዋል፡፡

ባለፉት ወራት ደግሞ የሁቲ ከፍተኛ አመራሮች በቀድሞ የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሚኒ የቀብር ሥርዓት እንዲገኙ ለማድረግ ከቴህራን የተላከውን አውሮፕላን ሳዑዲ በአየር ክልሏ እንዳያልፍ መከልከሏን ተከትሎ ቡድኑ ከሪያድ ጋር ግጭት ውስጥ ገብቶ ቆይቷል፡፡

አማፂያኑ ሳዑዲ ለፈፀመችው የአየር ክልል ክልከላ አፀፋም ቡድኑ የሳዑዲ ዓረቢያ የባህር ሀይል በቀይ ባህር እንቅስቃሴ እንዳያደርግ ገደብ በመጣል በሳዑዲ መርከቦች ላይ ጥቃት የፈፀሙ ሲሆን÷ ሪያድም በርካታ አፀፋ ሰጥታለች፡፡

በሁቲ አማፂያን እና በሳዑዲ ዓረቢያ በተከሰተው ግጭት ምክንያት በጂቡቲ፣ ኤርትራ እና የመን አዋሳኝ በቀይ ባህር የሚያልፉ መርከቦች ከፍተኛ የደህንነት ስጋት እንደገጠማቸው ተመላክቷል፡፡

ዓለም አቀፉ የንግድ ደህንነት ተቋም ኬፕለርን ጠቅሶ ሬውተርስ እንደዘገበው÷ ቡድኑ ገደብ ከመጣሉ በፊት በባብ ኢል መንዳብ የንግድ መስመር በቀን 50 መርከቦች ያልፉ የነበረ ሲሆን ከክልከላው በኋላ ግን ወደ 32 ዝቅ ማለቱን ጠቁሟል፡፡

ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ደህንነት እንዲጠበቅ እና የመርከቦች ደህነነት እንዲረጋገጥ የቀይ ባህር ይዞታ እና የባህር በር ጥያቄ ማቅረቧ ይታወሳል፡፡

አማፂያኑ በቀይ ባህር ቀጣና የሚፈፅሙት ጥቃት የንግድ መርከቦችን እንቅስቃሴ ከመግታት ባለፈ ጂቡቲ እና ኤርትራን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ደህንነት እና የኢኮኖሚ ትስስር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን ያስከትላል፡፡

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላም እና ጸጥታን ለማረጋገጥ፣ ድንበር ዘለል ሽብርተኝነትን ለመከላከልና በሕግ ማዕቀፍ ለመቆጣጠር የቆየ ሰፊ ልምድ አላት።

የአፍሪካን ህብረት እና የምስራቅ አፍሪካ የደህንነት ትብብሮችን በመጠቀም ከቀጣናው ሀገራት ጋር በቅንጅት እየሰራች ሲሆን÷ በአፍሪካ ህብረት እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥላ ስር በቀጣናው በሚደረጉ የሰላም ማስከበር ዘመቻዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ አድርጋለች።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ምላሽ ካገኘ እና ኢትዮጵያ የቀይ ባህር አጋር ከሆነች መሰል የሽብር ጥቃቶችን በመመከት እና የዓለም የንግድ እንቅስቃሴን በማሳለጥ ረገድ ሚናዋን ትወጣለች፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.