Fana: At a Speed of Life!

ከፅንሰ-ሃሳብ እስከ አህጉራዊ የመሪነት ሚና:- ዲጂታል ኢትዮጵያ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መረጃ በከፍተኛ ፍጥነት በሚበራከትበትና ዓለም በቴክኖሎጂ ወደ አንዲት መንደር በተቀየረችበት በዚህ ዘመን፣ ፍጥነትና የቴክኖሎጂ ዝግጁነት የብሔራዊ ህልውና እና የዕድገት መለኪያ ሆነዋል።
ይህን የዘመኑን እውነታ ቀድማ የተረዳችው ኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞዋን ለራሷ ሃገራዊ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም አርአያ በሚሆን መልኩ በጥንካሬ እያፋጠነች ትገኛለች፡፡
የሀገሪቱን የቴክኖሎጂ መሰረት የጣለው «ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025» ኢኒሼቲቭ በስኬት ተጠናቆ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ «ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030» ስትራቴጂ የተሸጋገረበት አሁናዊ ማዕቀፍ ውስጥ እንገኛለን፡፡
ትናንት በሃሳብ ደረጃ ብቻ የነበሩ እንደ ሳይንስ ሙዚየም፣ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ እና የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ያሉ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ማዕከላት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሙሉ ተግባር መሸጋገራቸው ሀገሪቱ ለያዘችው የትራንስፎርሜሽን እቅድ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል፡፡
«ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030» በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣ ሁሉን አካታችና ሉዓላዊ የዲጂታል ኢኮኖሚ የመገንባት ትልቅ ብሔራዊ ራዕይ ይዞ የተነሳ ነው፡፡
ይህም የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሂደት በብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) የዜጎችን የመታወቅ መብት ማረጋገጥን፣ ያለጥሬ ገንዘብ የሚከናወኑ የዲጂታል ክፍያዎችን ማስፋፋትን እና እንደ «መሶብ» ያሉ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶችን በተቀናጀ የኔትዎርክ መረብ ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል ማሸጋገርን ያለመ ነው።
መረጃ የዘመኑ ዋና ሀብት ነው፤ ዓለም የምትመራውም በዚህ ሀብት ትክክለኛ አጠቃቀም ነው፡፡
ኢትዮጵያ ይህን የዓለም አቀፍ የመረጃ መስመር ለመቀላቀል ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ የ4ኛ እና የ5ኛ ትውልድ የኢንተርኔት መረቦችን እያሰፋች ትገኛለች፡፡
ሆኖም የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት መዘርጋት ብቻውን ሙሉ አይሆንም፤ የሰው ሀይል ልማት እና የዲጂታል ክህሎት ግንባታ የትራንስፎርሜሽኑ ዋና አካል ናቸው፡፡
ለዚህም የ«5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች» ስልጠና ፕሮግራምና ሌሎች የአጭር ጊዜ ስልጠናዎች ዜጎችን ከቴክኖሎጂው ጋር የማዋሃድና የሰው ሰራሽ አስተዋፅኦን የማሳደግ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡
በሌላ በኩል የአካባቢውን ባህልና ቋንቋ ያገናዘበ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ላይ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ከሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ጋር የተጣጣመና እንደ «ChatGPT» ወይም «DeepSeek» ያሉ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሞዴሎችን የሚተካ «መላ» የተሰኘ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ስራ ላይ አውሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለፁት ፥ ቴክኖሎጂ በሲቪል ሰርቪስ፣ በሕግ ማስከበር፣ በመከላከያ፣ በሚዲያ፣ በግብርና እና በኢንዱስትሪ ዘርፎች የዕለት ተዕለት አሰራርን ለማፋጠንና ምርታማነትን ለማሳደግ እየዋለ ይገኛል፤ ይህም በእውቀት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ለመገንባት ጠንካራ መሰረት ጥሏል፡፡
በእመቤት ሲሳይ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.