ቃልን በተግባር
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19 ፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በመገጭ ግድብ ላይ ነፍስ የዘራው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ውሳኔ የመደመር መንግሥት ፕሮጀክቶችን ከመጀመር ባለፈ በተያዘላቸው ጊዜና በሚፈለገው ጥራት ስለማጠናቀቁ ምስክር ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ከአማራ ክልል የልማት ጥያቄዎች መካከል የመስኖና የመጠጥ ውሃ ጉዳይ አንኳር መሆኑን ማንሳታቸው ይታወሳል።
በተለይም ጎንደር ላይ ያለውን ከፍተኛ የመጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ እና ከመስኖ አንጻር ለ18 ዓመታት ተጓትቶ የቆየውን የመገጭ ግድብ ለማጠናቀቅ ብዙ ቢሊየን ብር ወጥቶባቸው የማይናቅ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
የቆየበትን ረጅም ቆይታ፣ የህዝቡን ጥያቄ እና ያንን ለመመለስ የተሄደበት መንገድ ቀላል ግምት የሚሰጠው እንዳልሆነ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መገጭ አሁን ላይ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኝና በቅርቡ ሥራ የሚጀምር መሆኑን በወቅቱ አብስረዋል።
ታዲያ ቃልን በተግባር የሚተረጉመው የመደመር መንግሥት ለበርካታ ዓመታት ሲጓተት የቆየውን የመገጭ ግድብ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በከፍተኛ ክትትልና ርብርብ ለትንሳኤው እንዲቀርብ አስችሏል።
በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በተደረገለት ከፍተኛ ክትትልና ርብርብ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 94 በመቶ መድረሱ ተገልጿል፡፡
የግድቡ ሥራ በአሁኑ ወቅት ጥራቱን ጠብቆ በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወነ ሲሆን፤ በቀጣይ ጥቂት ወራት ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በአሁኑ ወቅት የግድቡ የመስኖ ውሃ መቆጣጠሪያ ግንባታ እንዲሁም ተያያዥ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎችም ተጠናቅቀዋል።
ግድቡ አሁን ላይ 33 ሚሊየን ሜትር ኪውብ ውሃ የያዘ ሲሆን፤ በተገነቡት የመስኖ ውሃ መውጫዎች አማካኝነት በቀን 5 ሚሊየን ሜትር ኪውብ ውሃ መውጣት ጀምሯል፡፡
ከግድቡ ግንባታ ጎን ለጎን የንፁህ መጠጥ ውሃ የመስመር ዝርጋታ ስራ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፤ የውሃ ማማ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራውም በመጠናቀቅ ላይ ነው።
አሁን የሚቀረው የ6 በመቶ ስራ ብቻ በመሆኑ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አረጋግጠዋል።
የመገጭ ግድብ ሲጠናቀቅ 17 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ የማልማት አቅም ያለው ሲሆን፤ በተጨማሪም የጎንደር ከተማን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር እንደሚቀርፍ ይጠበቃል።
በሶስና አለማየሁ