የቤት ልማትን ወደ ዘመናዊና ፈጣን አማራጮች ማሸጋገር ተችሏል – ረሻድ ከማል (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተደረገው ተቋማዊ ማሻሻያ የቤት ልማትን ወደ ዘመናዊ እና ፈጣን አማራጮች ማሸጋገር ተችሏል አሉ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል (ዶ/ር)፡፡
የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የማኔጅመንት አባላት የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽንን ተቋማዊ ማሻሻያ እንዲሁም በቤት ልማትና በሥራ አፈጻጸም ዘርፎች ያስመዘገባቸውን ውጤቶች ጎብኝተዋል፡፡
ረሻድ ከማል (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ ተቋሙ በ50 ዓመታት ጉዞው ያጠናከረውን ተሞክሮ ከተቋማዊ ማሻሻያው ጋር በማጣመር የቤት ልማትና የገቢ ማሳደጊያ ሥራዎችን እያስፋፋ ነው፡፡
ኮርፖሬሽኑ ባከናወነው የማሻሻያ ሥራ የፒያሳና የጎልድ ሳይት ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ወደ አገልግሎት መግባታቸውን አስረድተዋል፡፡
ከደንበኞች ጋር በትብብር የተገነቡ የንግድ ቤቶች ወደ ኪራይ አገልግሎት መግባታቸውን እና ተጨማሪ ገቢ ማስገኘት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
ማሻሻያው ተቋሙን ከቀድሞ የተጓተተ አሰራር በማላቀቅ የአፈጻጸም ባሕሉ እንዲሻሻል፣ የንብረትና የቤት አስተዳደሩ እንዲዘምን፣ የገቢ ምንጮች እንዲስፋፉና በውጤት ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑ ማስቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም በቤት ልማት፣ በገቢ ዕድገት፣ በአፈጻጸም አቅምና በዘመናዊ የቤት አስተዳደር ሥርዓት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
ዘመናዊ የ3ዲ ግንባታ ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት የሙከራ ቤቶችን መገንባት መጀመሩን ጠቁመው ÷ በተከናወኑ ሥራዎች ተቋሙ በውስጣዊ አሰራር ብቻ ሳይወሰን የቤት ልማትን ወደ ዘመናዊና ፈጣን አማራጮች ማሸጋገሩን አብራርተዋል፡፡
የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቸሩጌታ ገነነ በበኩላቸው ÷ ሚዲያ የሀገርና መንግሥት ግንባታን ከማጠናከር፣ የልማት አቅጣጫዎችን ከማስፋትና በተቋማት የሚመዘገቡ ተጨባጭ ለውጦችን ለሕዝብ በማስተዋወቅ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ያካሄደው ተቋማዊ ሪፎርም ከተቋሙ ውስጣዊ አሰራር ለውጥ ባለፈ የመንግሥትን የቤት ልማት አቅጣጫ በተግባር የሚደግፍ ውጤት ማስገኘቱን ገልፀዋል፡፡
ተቋሙ በሪፎርም ሒደቱ የወሰዳቸው የአሰራር ማሻሻያዎች፣ የንብረትና የቤት አስተዳደር ልምዶች፣ የገቢ ማሳደጊያ አቅጣጫዎችና በውጤት ላይ የተመሠረተ የአፈጻጸም ባሕል መገንባቱ ለሌሎች ተቋማት የሚጋራ ተሞክሮ መሆኑን አውስተዋል፡፡
የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የማኔጅመንት አባላት÷ ጉብኝቱ የሁለቱን ተቋማት የልምድ ልውውጥና ትብብር በማጠናከር የሀገር ግንባታን እንዲሁም የልማት ሥራዎችን በጋራ ለማከናወን ጉልህ ሚና እንዳለው አብራርተዋል፡፡