Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለው የሪፎርም እርምጃ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው – አይ ኤም ኤፍ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለው የሪፎርም እርምጃ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው አለ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ።

በኢትዮጵያ ገቢዎች ሚኒስቴር እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ተወካዮች መካከል የማጠቃለያ ስብሰባ ተካሂዷል።

በዚህ ስብሰባ ላይ የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ውሃብረብ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የሪፎርም አጀንዳዎቿን ለማስቀጠል እና አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገቷን ለማጠናከር ያለሙ ቁልፍ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች።

የሪፎርም ስራዎቹ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ እና በተለያዩ ዘርፎች የሀገሪቱን አፈጻጸም ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ገልጸው ይህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጠንካራ አመራር እና ድጋፍ ሰጪነት እየተተገበረ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

ሚኒስቴሩ የገቢ አሰባሰብን ለማጠናከር እና የሀገር ውስጥ ሀብት የማንቀሳቀስ አቅምን ለማሳደግ የተቀረጹ በርካታ መሠረታዊ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) የገቢ አስተዳደር ምክትል የክፍል ኃላፊ ሪበካ ስፓርክማን በበኩላቸው፤ ሀገሪቱ እያከናወነች ያለችውን የሪፎርም ሥራዎች አድንቀዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የሪፎርም እርምጃዎች እና እቅዶች ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገትና ለሰፊ የልማት አጀንዳ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የማድረግ አቅም እንዳላቸው ገልጸው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የኢትዮጵያን የለውጥ ጥረቶች ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

በውይይቱ በገቢዎች ሚኒስቴር እና በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት መካከል ያለውን ትብብር ለማሳደግ፣ የሀገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብን ለማጠናከር እና ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማስፋፋት መግባባት ላይ መደረሱን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.