ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ምልከታ አደረጉ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና መስሪያ ቤት ተገኝተው የተቋሙን የሥራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው በፓስፖርት ህትመት፣ በውጭ ዜጎች አገልግሎትና አጠቃላይ የተቋሙን የአገልግሎት አሰጣጥ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በልዩ የሪፎርም ትግበራ ላይ የሚገኘው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፤ አሰራሩን በማዘመን የተሳለጠ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
አገልግሎቱ በበጀት ዓመቱ በአየርና በድንበር ለ7 ነጥብ 2 ሚሊየን ገቢና ወጪ መንገደኞች አገልግሎት የሰጠ ሲሆን፤ ፓስፖርትና ቪዛን ጨምሮ ከተለያዩ አገልግሎቶች ከ42 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ችሏል፡፡
በብቁ የሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ ራሱን በማደራጀት የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት፣ የቪዛ፣ የጉዞ ሰነዶች፣ ለውጭ ዜጎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን እንዲሁም የአየርና የመሬት ድንበር ቁጥጥርን ጨምሮ በርካታ ተግባራትን በውጤታማነት እያከናወነ ነው።
ይህም የመደመር መንግሥት በልዩ መርህና ትግበራ የያዘውን ዜጎችን ያከበረ የሀገርን እድገት የሚያስቀጥል ቀልጣፋና ተደራሽ አገልግሎት በመስጠት በኩል ልዩ ትርጉም አለው።
ተቋሙ ተደራሽነቱን ለማስፋት የአገልግሎት መስጫ ቅርንጫፎቹን ወደ 23 ከፍ ማድረግ የቻለ ሲሆን፤ ከ1 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ የውጪ ሀገር ዜጎች አገልግሎት ሰጥቷል።
በለይኩን ዓለም