የመጀመሪያውን የተለየ የቤት መግዣ ብድር መልሶ ማጠናከሪያ ኩባንያ ለማቋቋም የሚያስችል የትብብር ማዕቀፍ አከናውነናል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገራችን የመጀመሪያውን የተለየ የቤት መግዣ ብድር መልሶ ማጠናከሪያ ኩባንያ ለማቋቋም የሚያስችለውን ታሪካዊ የትብብር ማዕቀፍ አከናውነናል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ፥ በሀገራችን የመጀመሪያውን የተለየ የቤት መግዣ ብድር መልሶ ማጠናከሪያ ኩባንያ ለማቋቋም የሚያስችለውን ታሪካዊ የትብብር ማዕቀፍ አከናውነናል ብለዋል።
ስምምነቱ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC) መካከል መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በ100 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር ካፒታል የተቋቋመው እና በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ደግሞ 200 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ አስተዋፅኦ የሚያደርግበት ይህ ተቋም፤ በባንክ ዘርፋችን ውስጥ የጥሬ ገንዘብ ፍሰት አለመመጣጠንን የሚቀርፍ እና በመላው ኢትዮጵያ ተደራሽ የሚሆን የቤት መግዣ ብድር ፋይናንስን የሚያስገኝ ይሆናል ሲሉም አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ይህ አጋርነት በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገነቡና የኢትዮጵያውያንን ክብር የጠበቁ 1.5 ሚሊዮን ቤቶችን ለማቅረብ ቁልፍ ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ የግል ዘርፉን ተሳትፎ ለማስፋት ያስቀመጥነውን ግብ የሚያሳካ ወሳኝ ርምጃ ነው ሲሉም አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ፈጣን፣ ጠንካራ እና ሁሉንም ያካተተ ኢኮኖሚ መገንባቷን ትቀጥላለች ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።