ባለፉት አምስት ዓመታት የፖለቲካ ምሕዳሩን ለማስፋት የተከናወኑ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት አስገኝተዋል – አቶ ከማል ሃሺ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት አምስት ዓመታት የመገፋፋትና የሴራ ፖለቲካን ወደ ሃሳብ የበላይነት ለማሸጋገር የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች አስመዝግበዋል አሉ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባልና የምክር ቤቱ ጉዳዮች አማካሪ ኮሚቴ አባል አቶ ከማል ሃሺ።
አቶ ከማል ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት÷ የኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ረጅም እድሜ ያለውና የተለያዩ የሥርዓት ለውጦችን ያስተናገደ ቢሆንም የስክነትና የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል እጥረት ግን ይስተዋልበታል፡፡
በፖለቲካው ውስጥ የነበረው መጠላለፍ እና ለሕዝብና ለሀገር ከመቆም ይልቅ ለጊዜያዊ ሥርዓት የማደላት አባዜ ጠንካራ ሀገራዊ ተቋማት እንዳይገነቡ አድርጓል ብለዋል።
ይህም በኢኮኖሚው ላይ ምዝበራን፣ የሃብት ብክነትን እና የልሂቃንን ስደት ያስከተለ ሲሆን ÷ ማህበራዊ መስተጋብሩን በማላላት ረገድም ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል ነው ያሉት።
ይሁን እንጂ ባለፉት አምስት ዓመታት ከተከናወነው የፖለቲካ ለውጥ በኋላ ሀገሪቱን ወደ ሃሳብ የበላይነት ለማምጣት ትኩረት ተሰጥቶ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ለአብነትም የተለያዩ አቋም ያላቸው የፖለቲካ ኃይሎች በነፃነት ወደ ሀገራቸው ገብተው በሃሳብ እንዲፎካከሩ መደረጉን ጠቅሰዋል።
ይህም የመደመር ዕይታ ልዩነትን አቅፎ የጋራ ሀገራዊ አንድነትንና ብዝኃነትን ማዕከል ያደረገ አዲስ የፖለቲካ ባህል መፍጠሩን አብራርተዋል።
በቀደሙት ሥርዓቶች «አጋር» ተብለው ይጠሩ የነበሩት አካባቢዎች በሀገር ጉዳይ ላይ ሙሉ ውክልናና ውሳኔ ሰጪነት ተነፍገው እንደነበር ያነሱት አቶ ከማል ÷ አሁን ላይ ያ ዘመን ማብቃቱን አስረድተዋል።
እነዚህ ክልሎች አሁን በራሳቸው ጉዳይ ሙሉ በሙሉ የመወሰን መብታቸው ከመከበሩ ባሻገር እንደ ማዳበሪያና ጋዝ ልማት ያሉ በቢሊየን የሚቆጠሩ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የሚከናወኑባቸውና በሀገሪቱ የወደፊት ዕድል ላይ እኩል የመወሰን አቅም ያገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የሃሳብ የበላይነትን በተግባር ለማረጋገጥ በተካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ገዢው ፓርቲ ሙሉ ስልጣን የመያዝ እድል እያለው የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች በፌዴራልና በክልል የካቢኔ አባል በመሆን ትላልቅ ተቋማትን እንዲመሩ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
በቅርቡ በተካሄደው ምርጫም ተፎካካሪዎች ሰፊ ተሳትፎ እንዲኖራቸውና የተሻለ ወንበር እንዲያገኙ እድል የሚያሰፋ አሰራር መዘረጋቱን ገልጸው÷ ይህም በምክር ቤት ውስጥ የተለያዩ ድምፆች እንዲሰሙ የሚያስችል አቅም መፍጠሩን አብራርተዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ያሉ ገለልተኛ ተቋማት መመሥረታቸውና የቀደመውን የመሳሪያ ውጊያ ወደ ምክክር መድረክ እንዲሸጋገር ማድረጋቸው የዚሁ የሃሳብ ፖለቲካ ፍሬ መሆኑን ጠቁመዋል።
አሁንም የተጀመረው የሰለጠነ የፖለቲካ ጉዞ ግቡን እንዲመታ ከሀገሪቱ የፖለቲካና የአካዳሚክ ልሂቃን ትልቅ ሚና እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።
ልሂቃኑ ሁልጊዜ በመተቸትና በጎራ መከፋፈል ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ ጥናቶችን በማድረግ፣ ገንቢ ሃሳቦችን በማፍለቅና አስፈጻሚውን አካል በእውቀት በመመገብ ለሀገር ልማት፣ ሰላምና ብልጽግና የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በዮናስ ጌትነት