በመዲናዋ በመስከረም ወር ለሚከበሩ በዓላት በቂ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመት፣ መስቀል እና ኢሬቻ በዓላት በቂ የፍጆታ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለከተማዋ ነዋሪዎች እየቀረቡ ነው አለ የአዲስ አበባ ኀብረት ሥራ ኮሚሽን፡፡
ዋና ኮሚሽነሯ ሽታዬ መሀመድ በሰጡት መግለጫ፤ የገበያ ጥናትን መሠረት በማድረግ በበዓላት ወቅት በገበያ ላይ የሚፈጠረውን ፍላጎት በመለየት በቂ የፍጆታ ምርቶች እንዲቀርቡ በስፋት ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
ኮሚሽኑ ከአምራቾች፣ ከአስመጪዎች፣ ከዩኒየኖችና ከተለያዩ የኀብረት ሥራ ማህበራት ጋር በመተባበር የምርት ትስስር በመፍጠር ምርቶች በበቂ መጠን እንዲቀርቡ አድርጓል ብለዋል፡፡
እነዚህ ምርቶች በከተማዋ በሚገኙ 700 ዘመናዊ የሸማች ኀብረት ሥራ ማህበራት ሱቆችና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ በአዲስ ዓመት ኤግዚቢሽኖችና ባዛሮች፣ በቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች እየቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርቡት እነዚህ ምርቶች የነዋሪዎችን የበዓል ፍላጎት ለማሟላት፣ የኑሮ ውድነትን ለማቃለልና ገበያውን ለማረጋጋት ከፍተኛ ሚና አላቸው ብለዋል።
በተጨማሪም በበዓሉ ወቅት 274 ማህበራት ልኳንዳ ሥጋ ቤቶች ሥጋን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እንዲያቀርቡ ዝግጅት መደረጉን ገልጸው፤ ይህም በበዓሉ ወቅት የሚታየውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር አስተዋፅኦ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
ህብረተሰቡ ምርቶቹን ከኀብረት ሥራ ማህበራት ሱቆች፣ ከኤግዚቢሽንና ባዛር ማዕከላት እንዲሁም ከቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በመግዛት በተመጣጣኝ ዋጋ ተጠቃሚ እንዲሆን ጥሪ ማቅረባቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል።