Fana: At a Speed of Life!

የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎትን የሚያሳልጥ ዲጂታል መተግበሪያ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ደንበኞች ባሉበት ሆነው የተቋሙን አገልግሎቶች በማንኛውም ሰዓት ማግኘት የሚያስችል አዲስ ዲጂታል መተግበሪያ ይፋ አድርጓል።

የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አብዱልበር ሸምሱ (ኢ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ አዲሱ የዲጂታል መተግበሪያ አገልግሎቶችን ቀልጣፋ፣ ተደራሽና ዘመናዊ በማድረግ ክፍተቶችን ለማረምና የሀገርን ተጠቃሚነት የሚያሳድግ ነው፡፡

የአገልግሎት አሰጣጡ ዲጂታል መሆን የጊዜ አጠቃቀምን በማሻሻል አገልግሎት ፈላጊዎች ላይ የሚፈጠሩ አሰልቺ ሂደቶችን በመቅረፍ ጊዜና ቦታ ሳይገድባቸው እንዲጠቀሙ ያስችላል ነው ያሉት።

ዲጂታል መተግበሪያው በ7ቱም ቀናት ለ24 ሰዓት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) በበኩላቸው፥ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ልማት ለማፋጠን ከሚያስፈልጉ ዋና አሳላጮች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን መጪውን የብልፅግና መዳረሻ ዕውን ለማድረግ በዋናነት ለሎጂስቲክስ ዘርፉ የባሕር በር ባለቤትነትን ማሳካት ግድ እንደሚል አንስተዋል።

ይፋ የተደረገው የዲጂታል አገልግሎት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ጉዞን ለማሳካት የተያዙ ግቦች ዕውን እንዲሆኑ የራሱን ሚና የሚወጣበት ምዕራፍ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም በዲጂታል ምህዳር ተጠቃሚነት የሰነዶች ደህንነት እንዲጠበቅ በማስቻል በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ አሰልቺ ሂደቶችን ለመቅረፍ እንደሚረዳም ነው የተገለጸው።

በአሽናፊ ሽብሩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.