Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የሕክምና ልህቀት ማዕከል ለመሆን የጀመረችው ጉዞ ትክክለኛ መስመር ላይ ይገኛል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በአፍሪካ የሕክምና ልህቀት ማዕከል እና የሕክምና ቱሪዝም መዳረሻ ለመሆን የጀመረችው ጉዞ ትክክለኛ መስመር ላይ ይገኛል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን በጤና እና በትምህርት እያገለገለ ያለውን የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅን የሥራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል፡፡

ጉብኝቱን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት ÷ የሆስፒታሉን ብቻ ሳይሆን የሃገራችንን የጤና ዘርፍ ወደ ከፍተኛ ምዕራፍ የሚያሸጋግረው አኩቴክ (ACCU-TECH) ዲያግኖስቲክ ላብራቶሪ ለሃገራችን የዘርፉ ልዩ መለያ እና አቅም ነው ብለዋል።

ዘመናዊው ላቦራቶሪ በአንድ ጊዜ በርካታ ሳምፕሎችን ከመቀበሉም በላይ ለተወሰነ ጊዜ ሳምፕሎችን በጥንቃቄ ለማቆየትም የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም በትምህርት ተቋሙ የስነተዋልዶ ጤና ልህቀት ማዕከልን፣ ለታካሚ እጅግ ምቹ የሆነውን የካንሰር የጨረር ህክምና ማዕከልን እና የአገልግሎት ነጻ የጥሪ ማዕከሉን መጎብኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ ከሆስፒታልነት በላይ የሰው ኃይል ልማትን፣ የልዩ ሕክምና አገልግሎትን፣ ምርምርንና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በአንድ ላይ ያቀናጀ ሀገራዊ የጤና ተቋም መሆኑን በጉብኝታችን አረጋግጠናል ነው ያሉት።

ሆስፒታሉ ከመላ ኢትዮጵያ እንዲሁም ከአፍሪካ ለሚመጡ ታካሚዎች የኩላሊት፣ የልብ እና መሰል ውስብስብ የጤና እክሎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂና ብቃት ባላቸው ሀኪሞቹ አክሞ በማዳን የብዙዎችን ህይወት መታደጉን ጠቁመዋል፡፡

የተቋሙ የህክምና አገልግሎት ኢትዮጵያ በአፍሪካ የሕክምና ልህቀት ማዕከል እና የሕክምና ቱሪዝም መዳረሻ ለመሆን የጀመረችው ጉዞ ትክክለኛ መስመር ላይ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ሆስፒታሉ ከሆስፒታል ወደ ጤና ከተማ ከኮሌጅ ወደ ሕክምና እና ጤና ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ የሚያደርገውን የልህቀት ጉዞ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.