በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 7 ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዛሬ በሦስተኛ ሳምንት እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር 7 ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ በአሰልጣኝ ኤንዞ ማሬስካ የሚመራው ማንቼስተር ሲቲ የፍራንክ ላምፓርዱን ኮቨንትሪ ሲቲን ያስተናግዳል።
ሁለቱን ተከታታይ ጨዋታዎች በማሸነፍ 6 ነጥብ መሰብሰብ የቻለው ማንቼስተር ሲቲ በሊጉ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት የገጠማቸውን ኮቨንትሪ ሲቲን በማሸነፍ የሊጉን ፉክክር ያጠናክራል ተብሎ ይጠበቃል።
በተመሳሳይ 11 ሰዓት ላይ ብሬንትፎርድ ከሰንደርላንድ፣ ብራይተን ከሊድስ ዩናይትድ፣ ፉልሃም ከክሪስታል ፓላስ እንዲሁም ኖቲንግሃም ፎረስት ከቶተንሀም ሆትስፐርስ ይገናኛሉ።
በዕለቱ ቀደም ብሎ ቀን 8፡30 ላይ በሴንት ጄምስ ፓርክ ኒውካስል ዩናይትድ ከቦርንሞውዝ ጨዋታቸውን ሲያደርጉ ምሽት 1፡30 ላይ ደግሞ ሃል ሲቲ እና አስቶን ቪላ ይፋለማሉ።
በሌላ በኩል ትናንት ምሽት በተካሄደ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 3ኛ ሳምንት ጨዋታ ሊቨርፑል ኢፕስዊች ታውንን 2 ለ 0 ማሸነፍ ችሏል። አምና ከኒውካስትል ወደ አንፊልድ የተዛወረው ስዊድናዊው አጥቂ አልክሳንደር አይዛክ ለሊቨርፑል ሁለቱን ግቦች አስቆጥሯል፡፡
በዮናስ ጌትነት