ከአገልግሎት ቅልጥፍና ባሻገር፥ የላቀ ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዛሬ ላይ ጣትን በምራቅ እያራሱ ገንዘብ ቆጥሮ የመስጠትና የመቀበል የዕለት ዕለት ተግባር እየቀረ ነው።
“ረዳት መልስ ስጠኝ” የሚለው የተለመደ የታክሲ ተሳፋሪ ጥያቄ ቀርቷል፤ ዛሬ በጉዟችን የምንሰማው “ረዳት ቴሌብር ንገረኝ” የሚል ሆኗል።
ከዝቅተኛ የታክሲ ታሪፍ እስከ መንደር ሱቆች፤ ከመካከለኛ እስከ ትልልቅ ንግዶች ክፍያ በዲጂታል አማራጮች መሳለጥ ከጀመረ ዋል አደር ብሏል።
በቴሌብር አልያም ሌሎች የዲጂታል ክፍያ አማራጮች ገዢ ለሸመታው፤ ተገልጋይም ለቀረበለት አገልግሎት በቅስበት ክፍያ ይፈጽማል።
በዲጂታል አማራጭ በፍጥነት እየተተካ ያለው የአገልግሎትና የሸመታ ክፍያ ልምምድ ለሀገራችን የፋይናንስ ስርዓት፣ አጠቃላይ ኢኮኖሚና ለሕዝቡ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው።
ክፍያ በዲጂታል ሲሆን፤ ሰዎች ሊገበያዩ፤ አልያም ያሻቸውን አገልግሎት ለማግኘት ገንዘብ በቦርሳቸው ሸክፈው ሌባ አየኝ አላየኝ እያሉ የሚሳቀቁበት የደህንነት ስጋት ያከትማል።
ጥሬ ገንዘብ ለማውጣት በባንኮች በመሰለፍ የሚባክነውን ጊዜ ይቆጥባል፤ እንግልትንም ያስቀራል።
በዲጂታል አማራጭ የሚከወኑ ክፍያዎች ተመዝግበው የሚቀመጡ በመሆናቸው ተገልጋዮችም ሆኑ አገልግሎት ሰጪዎች ወጪና ገቢያቸውን እንዲያውቁ ያስችላቸዋል።
በታክሲና በሰፈር ሱቆች ጭምር የምናደርጋቸው አነስተኛ የዲጂታል ክፍያዎች ከክፍያ ቅልጥፍና ባሻገር በሀገሪቱ የፋይናንስ ስርዓትና ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ለውጥ እያመጡ ይገኛሉ።
ቀደም ሲል ከባንክ ስርዓት ውጭ የነበሩ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በር ከፍቷል፤ ይህም የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው።
የፋይናንስ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ የዲጂታል ክፍያ ሌላኛው ፋይዳ የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ እድገት ነው።
በሰዎች እጅ የነበረ ጥሬ ገንዘብ ወደ ዲጂታል ሂሳብ በመግባቱ የባንኮች የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ያድጋል፤ ይህም ባንኮች ለልማትና ለንግድ የሚሆን የብድር አቅርቦት እንዲጨምሩ ያስችላቸዋል።
የዲጂታል ክፍያ መስፋፋት፤ ሰዎች በገንዘብ እንቅስቃሴያቸው ታሪክ መሰረት ከባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት ያለ ማስያዣ አነስተኛ ብድሮችን እንዲያገኙ ይረዳል።
የገንዘብ ማተሚያ ወጪ መቀነስ፣ የጥቁር ገበያና ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርን መግታት፣ የታክስ ገቢ ማደግ እንዲሁም የግብይት ፍጥነት የዲጂታል ክፍያ ስርዓት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያበረክተው ትሩፋት ነው።
ቴሌብር ከ60 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ደንበኞችን ያፈራ ሲሆን፤ በአጠቃላይ እስካሁን 9 ነጥብ 13 ትሪሊየን ብር የገንዘብ ዝውውር ተፈጽሞበታል።
በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት ብቻ በቴሌብር አማካኝነት የ4 ነጥብ 51 ትሪሊየን ብር ግብይት ተፈጽሟል።
ለአብነትም የቴሌብር ተጠቃሚዎችን ቁጥርና የገንዘብ ዝውውር መጠን ብንመለከት የዲጂታል ክፍያ አድማስ ምን ያህል እንደተስፋፋ ጥሩ ማሳያ ይሆናል።
ስልካችንን አንስተን የምንከፍላት እያንዳንዷ ሳንቲም የሀገሪቱን የፋይናንስ እንቅስቃሴ በዘመናዊ መሠረት ላይ እየገነባች እንደሆነ ማሳያ ናት።
በኃይለማርያም ተገኝ