Fana: At a Speed of Life!

ከቀላል የገንዘብ ማንቀሳቀሻነት እስከ ኢኮኖሚ ዋነኛ ሞተርነት – ቴሌብር

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ቴሌብር በኢትዮጵያ የዲጂታል ፋይናንስ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ እየጻፈ ይገኛል፡፡

መተግበሪያው በቀላል የሞባይል ገንዘብ ማንቀሳቀሻነት ወይም ሞባይል ዋሌትነት የጀመረውን ጉዞ በማስፋት ዛሬ ላይ ምሉዕ የዲጂታል ፋይናንስ ሥነ ምሕዳር መሆን ችሏል።

ቴሌ ብር ክፍያዎችን፣ የመክፈያና የገንዘብ መሰብሰቢያ ዘዴዎችን፣ የንግድ አገልግሎትን፣ የመንግሥት ክፍያዎችን፣ ቁጠባን፣ ብድርን፣ የሐዋላ አገልግሎትን እንዲሁም ዲጂታል ንግድንና ሌሎች ተጨማሪ እሴት የሚፈጥሩ አገልግሎቶችን በውስጡ በማካተት የሀገሪቱ ዲጂታል ኢኮኖሚ ዋነኛ አንቀሳቃሽ ሞተር በመሆን እያገለገለ ይገኛል።

ለዚህ ስኬት ደግሞ ከ33 ባንኮች፣ ከአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማትና ከቁጠባና ብድር የህብረት ስራ ማህበራት ጋር የተፈጠረው ጠንካራ ትስስር እንዲሁም ሰፊው የወኪሎችና ነጋዴዎች መስተጋብር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ይህም አቅም በጋራ የመስራት እሴትን በማጠናከር የሀገሪቱን የዲጂታል ፋይናንስ መሠረተ ልማት እና ተደራሽነት ይበልጥ አግዟል።

በየጊዜው የደንበኞችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያሳደገ የሚገኘው ይህ የፋይናንስ ሥነ ምህዳር በአጠቃላይ 60 ነጥብ 6 ሚሊየን ደንበኞችን ማፍራት ችሏል፡፡

በ2018 በጀት ዓመት ብቻ 8 ነጥብ 54 ሚሊየን አዳዲስ ደንበኞች መመዝገብ መቻላቸው ሕብረተሰቡ ለዲጂታል ፋይናንሲንግ ያለውን አዎንታዊ ምልከታ ማሳደግ እንዳስቻለ ያሳያል ።

የቴሌብር የግብይት እንቅስቃሴ ከፍተኛ ጭማሪ በማሳየት በሀገሪቱ የገንዘብ ዝውውር ላይ ትልቅ ድርሻ የያዘ ሲሆን ÷ በዚህም 2 ነጥብ 61 ቢሊየን ግብይቶችን አስተናግዷል፡፡ ይህም የታቀደውን 2 ነጥብ 09 ቢሊየን በማለፍ የዕቅዱን 124 ነጥብ 6 በመቶ አሳክቷል፡፡

በተጠናቀቀው 2018 በጀት ዓመት ብቻ በቴሌ ብር 4 ነጥብ 19 ትሪሊየን ብር ግብይት የተከናወነ ሲሆን÷ ይህም የታቀደውን 4 ነጥብ 51 ትሪሊየን ብር 92 ነጥብ 8 በመቶ ማሳካት ችሏል፡፡

ቴሌብር ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በአጠቃላይ 9 ነጥብ 13 ትሪሊየን ብር የሚገመት ግብይት የተከናወነበት መሆኑን የኢትዮ ቴሌኮም መረጃ ያመላክታል፡፡

በዚህ የፋይናንስ መንገድ ውስጥ 410 ነጥብ 7 ሺህ ወኪሎች እና 440 ነጥብ 1 ሺህ ነጋዴዎች አገልግሎቱን በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

እነዚህ ወኪሎች ደንበኞችን የመመዝገብ፣ ገንዘብ ገቢና ወጪ የማድረግ፣ የአየር ሰዓት የመሸጥ እና ክፍያዎችን የማስተናገድ ተግባራትን እንዲያከናውኑ በማስቻል አዳዲስ የሥራ እድሎችን በመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ያለዋስትና በሚሰጠው የዲጂታል ብድር አማካኝነት የበርካቶችን ችግር ሲቀርፍ÷ 19 ነጥብ 51 ቢሊየን ብር ለ5 ነጥብ 65 ሚሊየን ደንበኞች ተደራሽ ተደርጓል፤ በዚህም የዓመታዊ ዕቅዱን 87 ነጥብ 7 በመቶ አሳክቷል።

ቁጠባን ከማበረታታት አንጻር በ2018 በጀት ዓመት ብቻ የዲጂታል ቁጠባ መጠን ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን ደንበኞች 18 ነጥብ 75 ቢሊየን ብር የደረሰ ሲሆን÷ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ66 ነጥብ 9 በመቶ ከፍተኛ ዕድገትን ያሳያል።

በአጠቃላይ ቴሌብር የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ፣ የዜጎችን የፋይናንስ ተሳትፎ በማሳደግ እና የሀገሪቱን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ በማፋጠን ለኢትዮጵያ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መሠረታዊ እና ዋነኛ ሞተር መሆኑን አስመስክሯል።

በመልካም ፈቃዱ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.