ከሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የተገኙ ምክረ-ሃሳቦች በየፈርጁ እየተደራጁ ነው -የምክክር ኮሚሽን
አዲስ አበባ፣ጳጉሜን 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የተገኙ ምክረ–ሃሳቦች በየፈርጁ እየተደራጁ ነው አለ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን።
የኮሚሽኑ መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል
ኮሚሽኑ ከሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የተገኙ ምክረ–ሃሳቦችን በየፈርጁ በማደራጀት ላይ ይገኛል
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሐምሌ 01 ቀን – ነሐሴ 16 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤውን ሲያስተባብር መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ኮሚሽኑ በርካታ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ምክረ–ሃሳቦች ማሰባሰብ የቻለ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ለመመካከር ያሳዩት ቁርጠኝነት ውጤት ነው፡፡
ኮሚሽኑ በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 አንቀፅ 9 (10፣ 11፣ 12) በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት
የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ አጀንዳዎችን፣ የምክክሮቹን ሂደት፣ በምክክሮቹ የተገኙ ምክረ–ሃሳቦችን እንዲሁም ምክረ– ሃሳቦቹ በተግባር ላይ ሊውሉ የሚችሉበትን ሥልት የሚገልጽ ሰነድ በማዘጋጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለአስፈጻሚ አካሉ እና ለሌሎች የሚመለከታቸዉ የመንግስት አካላት አቅርቦ፤ ለሕዝብም ይፋ እንደሚያደርግ፤
መንግሥት ከሀገራዊ ውይይቶች የሚገኙ ምክረ–ሃሳቦችን በተግባር ላይ ለማዋል እንዲችል ግልፅ እና ተጨባጭ የሆነ ዕቅድ እንዲዘጋጅ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ፤ እንዲሁም
የምክረ–ሃሳቦቹን አፈፃፀም መከታተል የሚያስችል ሥርዓት እንደሚዘረጋ በአዋጁ ተደንግጓል፡፡
ይህንን መነሻ በማድረግ ኮሚሽኑ፦
በአሁኑ ሰዓት ከሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የተገኙ ምክረ–ሃሳቦችን በየፈርጁ በማደራጀት ላይ ይገኛል፤
በቀጣይ ምክረ–ሃሳቦቹን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀርባል፣
በመቀጠልም ምክረ–ሃሳቦቹን አግባብነት ባለው መንገድ ለሕዝብ ይፋ ያደርጋል፣
በመጨረሻም ምክረ–ሃሳቦቹን ለአስፈፃሚ በማቅረብ ተፈፃሚነታቸውን ይከታተላል፡፡