Fana: At a Speed of Life!

ትውልዱ በጋራ በመቆም የሀገርን ጽናት ማረጋገጥና ማስቀጠል አለበት

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አባቶቻችን በአንድነት ቆመው የጸናች ሀገርን እንዳስረከቡን ሁሉ የአሁኑ ትውልድ ሀገርን በሚያጸኑ የልማት ስራዎች በጋራ በመቆም የሀገርን ጽናት ማረጋገጥና ማስቀጠል አለበት አሉ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ እና የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የጽናት ቀንን እያከበሩ ነው፡፡

ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ጽናት በፈተና ጊዜ አለመሸነፍ፣ በችግር ውስጥ ተስፋን መጠበቅና የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ እስከ መጨረሻ መፈጸምና ማስፈጸም ነው፡፡

የጸናች ሀገር መሠረት የተቋማት ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን፤ የህዝብ አንድነት፣ ኃላፊነትና ተሳትፎ መሆኑን ጠቁመው÷ በመተጋገዝ፣ በትዕግስትና በቁርጠኝነት ችግሮችን መሻገር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ሀገርን ለማጽናት መስዋትነት እየከፈለ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት አክብሮታቸውን የገለጹት ዋና አዛዡ÷ ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ትኖራለች ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትልና የጸጥታ ኦፕሬሽን ዘርፍ ኃላፊ ተስፋዬ ደንድር በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያውያን ለጋራ ዓላማ የሚቆሙ እና በጽናት የሚኖሩ ህዝቦች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይም ኢትዮጵያውያን ታላቁን የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሀገር እንድንታሰራራና ወደ ብልጽግና ማማ እንድትሄድ የሚያስችሉ ውጤታማ ስራዎችን በጋራ እያሳኩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ሀገር የተገኙ ውጤቶችን ለማስቀጠል ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር ድህነትንና ተረጅነትን ታሪክ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.