ኢትዮጵያን ታላቅ ያደረጋት ሉዓላዊነት የተገነባው በልጆቿ ጽናት ነው – አቶ አሻድሊ ሀሰን
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያን ታላቅ ያደረጋት ሉዓላዊነት የተገነባው በልጆቿ ጽናት ነው አሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን፡፡
ጳጉሜን-3 የጽናት ቀን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በታሪኳ ያጋጠሟትን ፈተናዎች ተሻግራ ለዛሬ የደረሰችው በሕዝቦቿ የተባበረ የጽናት መንፈስ ነው፡፡
ዛሬም እንደታላቁ ሕዳሴ ግድብ ያሉ የልማት ድሎችን የማስመዝገባችን ምስጢር በፈተናዎች ያለመበገራችንና የጽናታችን ውጤት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሉዓላዊትና የተከበረች ሀገር ሆና የቀጠለችው በአንድ ትውልድ ብቻ አይደለም ያሉት አቶ አሻድሊ፤ ይልቁንም በትውልድ ቅብብሎሽ በተሻገረ የአብሮነት ጽናት መሆኑን ገልጸዋል።
ዛሬም ከቀደመው ትውልድ የተረከብናትን ከመጠበቅ ባሻገር የበለጠ የተከበረች እና የበለጸገች ሀገር ገንብተን ለትውልድ የማሻገር አደራችንን መወጣት አለብን ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
እንደሀገርም ሆነ እንደክልል በየዘርፉ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ የተጀመሩ የሰላም፣ የልማት፣ የመልካም አስተዳድር እና የቴክኖሎጂ ሥራዎችን ለማጠናከር የአሁኑ ትውልድ የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡