Fana: At a Speed of Life!

የስንዴ ምርት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ፤ የግብርናው ዘርፍ እመርታ ማሳያ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የስንዴ ፕሮግራም ምርታማነትን በመጨመር፣ የመስኖ ሥርዓትን በማስፋትና የዘር አቅርቦት ሥርዓትን በማጠናከር የሀገሪቱን በምግብ ራስን የመቻል ጉዞ አጠናክሯል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አለማምረት በሌሎች ሰዎች በጎ ፈቃድ ላይ እንድንወድቅና ለተለያዩ ችግሮች እንድንጋለጥ ያደርገናል ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

በተጨማሪም እርዳታን የሚቀበል፣ ምግብ የሚለምንና ፍላጎቱን በሙሉ በገቢ ምርት ላይ ብቻ የመሰረተ ሀገር ነጻና ሉዓላዊ ነኝ ማለት አይችልም ማለታቸው ይታወሳል፡፡

ከውጪ በሚደረግ የእርዳታ ሂደት ውስጥ የውሳኔ አቅምን ማሳጣት የሚጠበቅ በመሆኑ፤ ኢትዮጵያ ከተረጂነት በመውጣት በምግብ ራሷን ለመቻል በምታደርገው ሂደት ውስጥ የስንዴ ምርትን በ10 ዓመቱ የግብርና ልማት ምርት ውስጥ አንዱ አድርጋዋለች፡፡

የስንዴ ምርት የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና ለአርሶ አደሩ የገቢ ምንጭ ከመሆኑ ባሻገር፤ ስንዴን ከውጪ ማስገባትን በማስቀረትና በሀገር ውስጥ እንዲመረት በማስቻል ለሀገሪቷ የውጪ ምንዛሬ ችግርን ለመቅረፍ ሚናው ትልቅ ነው፡፡

በስንዴ ምርት ራስን መቻል ያስፈልጋል ሲባል እንደ ዘበት ይታይ የነበረ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ የሚቻል የማይመስለውን ሁሉ የማሳካት አቅም ያላት በመሆኗ ዛሬ በዓመታዊ የስንዴ ምርት ከአፍሪካ ቀዳሚ ስፍራ ላይ ትገኛለች፡፡

ይህም እመርታ የግብርናውን ዘርፍ በቴክኖሎጂ በማዘመን፤ ከዚህ ቀደም ጥቅም ላይ ያልዋሉ የእርሻ መሬቶች ወደ ምርት እንዲገቡ በማድረግ ረገድ ሚናው የጎላ ነው፡፡

እንዲሁም ዝናብን ከመጠበቅ የበጋ መስኖ ስንዴን የማልማት ኢኒሼቲቭ በመጀመርና በራስ አቅም ራስን የመለወጥ ጥረት የመጣ ተግባራዊ ውጤት ነው፡፡

ቤተልሔም ግርማ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.